ቀጥታ፡

በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ብቁ አትሌቶችን ለማፍራት እየተሰራ ነው ---የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ

ደሴ ሐምሌ 3/2015 (ኢዜአ)  ብቁ ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተወካይ አቶ ቢልልኝ መቆያ ገለፁ፡፡

በተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገር ደረጃ ተወዳድረው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶች ዛሬ በደሴ ከተማ እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮምቴ ተወካይ አቶ ቢልልኝ መቆያ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት ስመጥርና ብቁ ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላትን በመደገፍና በማጠናከር የተሻሉ አትሌቶችን ለማፍራት ከአመራሩና ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በስፖርቱ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ከማጠናከር ባለፈ በዓለም መድረክ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎች በቅንጅት እየተሰሩ መሆኑንም አቶ ቢልልኝ አመልክተዋል።

በተለያዩ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ማዕከሉ 92 ሜዳሊያዎችን አግኝቶ ውድድሩን በአንደኝት ማጠናቀቁን የገለጹት ደግሞ የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሃመድ አባተ ናቸው።

በአማራ ክልል እና በሀገር ደረጃ ያሉ ማዕከላት በተሳተፉባቸው ውድድሮች ማዕከሉ 35 ወርቅ፣ 34 ብር እና 23 ነሃስ ማግኘቱን ጠቅሰው፤ "ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ የዓለም ሀገራት መወዳደር የሚችሉ አትሌቶችንም ማፍራት ተችሏል" ብለዋል።


 

"እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ማዕከሉ ትኩረት አግኝቷል" ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ቀጣይም የተጀመሩ ሥራዎችን በማስቀጠል ተወዳዳሪ አትሌቶችን የማፍራት ስራው እንደሚጠናከር አመልክተዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል እገዛ እያደረገ መሆኑንና ይህም ስመጥርና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። 

ማሰልጠኛ ማዕከሉ በየዓመቱ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ በማዕከሉ ከክልል ባለፈ ሀገር ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶችን ማፍራት መቻሉን አድንቀዋል።

"በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ማዕከሉ ያፈራቸው 6 አትሌቶች ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ የዓለም ሀገራት ውጤት በማስመዝገባቸው ዩኒቨርሲቲው ኩራት ይሰማዋል" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ለማሰልጠኛ ማዕከሉ በዩኒቨርሲቲው የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

አትሌት ሰላም ምህረት በበኩሏ በ2013 ዓ.ም የተንታ አትሌቲክስ ማዕከልን በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል መቀላቀሏንና ባደረገችው ጠንካራ ዝግጅትም ውጤት ማስመዝገቧን ገልጻለች።

በሀገር ውስጥ በተካሄዱ ውድድሮች 3 የወርቅ ሜዳሊያ ከማምጣት ባለፈ በዛምቢያ በተካሄደ ውድድር 6ኛ ደረጃ መውጣቷን አስታውሷ፣ ለቀጣይ ውድድሮች ዝግጅት እያደረገች መሆኗን ተናግራለች።

ሌላው አትሌት ብዙዓለም ብናልፍ በበኩሉ በ5 ሺህ ሜትር ሩጫ እየተወዳደረ መሆኑን ጠቁሞ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተካሄዱ ውድድሮች የብር ሜዳሊያ ማምጣቱን ተናግሯል።

"ጠንካራ ልምምድ በማድረግ ውጤት ማስመዝገብ ጀምረናል" ያለው ወጣቱ፣ "ዛሬ የተሰጠው እውቅና በቀጣይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ ከፍ ለማድረግ መነሳሳትን ይፈጥሯል" ብሏል።

በተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል 52 አትሌቶች የሚገኙ ሲሆን ውጤታማ ለሆኑ አትሌቶችም እንዳገኙት ውጤት ሙሉ የስፖርት ትጥቅና ከ2 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ተበርክቶላቸዋል። 

በእውቅናና ሽልማት መርሀግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን አመራችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም