ቀጥታ፡

በሱዳን እና በቀጣናው የሰላምና ደህንነት ላይ ለመምከር በኢጋድ የተቋቋመው የአራትዮሽ "ኳርቴት" የመሪዎች ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2015(ኢዜአ)፦ በሱዳን እና በቀጣናው የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ በኢጋድ የተቋቋመው የአራትዮሽ "ኳርቴት" የመሪዎች ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

በሱዳን የተፈጠረውን የእርስ በእርስ ግጭት በድርድር ለመፍታት በመሪዎች ደረጃ በአዲስ አበባ ውይይት ለማካሄድ መርሃ-ግብር ተይዟል።

የኬኒያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ(ዶ/ር) በኢጋድ የአራትዮሽ "ኳርቴት" የሱዳን እና ቀጣናዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች የመሪዎች ስብሰባ ለመሳተፍ  ትላንት ምሽቱን አዲስ አበባ ገብተዋል።


ፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባ ሲገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።


ቀደም ብሎም የጅቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሃመድ አሊ የሱፍ እና የሰብዓዊ ጉዳዮች እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ ማስተባበሪያ (ኦቻ) ዋና ፀኃፊ ማርቲን ግሪፍትስ አዲስ አበባ ሲገቡ በተመሳሳይ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።


የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በጅቡቲ ባካሄደው 14ኛ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ያሉበት የአራት አገራት "ኳርቴት" የተሰኘ ኮሚቴ በማዋቀር የሱዳንን ግጭት ለማስቆም ውክልና መስጠቱ የሚታወስ ነው።


የመፍትሔ አፈላላጊ የምክክር መድረኩም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ተፋላሚ ሃይሎችን የማደራደርና የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀላጠፍ ይሰራል።


የሰላም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው የሱዳን ጦር መሪ ጀኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃንን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ሌፍተናንት ጀነራል ሙሀመድ ሀምዳን ዳጋሎን (ሔሜቲ) በአስር ቀናት ውስጥ ለማነጋገር አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።


ኢጋድ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተክትሎም ሱዳን ላጋጠማት ወቅታዊ ችግር መፍትሔ ለመስጠትና በቀጣናዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ የአባል አገራት መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ይወያያሉ።


በውይይቱ ላይ የጅቡቲ ፕሬዝደንት እስማዔል ዑመር ጉሌህ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫኪር ማያርዲት እንዲሁም የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም