ቀጥታ፡

የሱዳንን ግጭት በድርድር ለመፍታት በኢጋድ የተወከሉ መሪዎች አዲሰ አበባ እየገቡ ነው

አዲስ አበባ ሐምሌ 2/2015(ኢዜአ)፦የሱዳንን ግጭት በድርድር ለመፍታት በኢጋድ የተወከሉ ሀገራት መሪዎች በውይይቱ ለመሳተፍ አዲሰ አበባ እየገቡ ይገኛሉ።

የሱዳንን የርስ በርስ ግጭት ለመፍታት ተፋላሚ ሀይሎችን ለማደራደር በነገው እለት በአዲስ አበባ በመሪዎች ደረጃ ውይይት ይካሄዳል።

የኬኒያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶም(ዶ/ር) በኢጋድ የአራትዮሽ "ኳርቴት" የሱዳን እና ቀጣናዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች የመሪዎች ስብሰባ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ሲገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቀደም ሲልም የጅቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሃመድ አሊ የሱፍና የሰብዓዊ ጉዳዮች እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ ማስተባበሪያ (ኦቻ) ዋና ፀኃፊ ማርቲን ግሪፍትስ አዲስ አበባ ሲገቡ ሚኒስትር ዴኤታዋ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ጅቡቲ ባካሄደው 14ኛ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ያሉበት የአራት አገራት "ኳርቴት" የተሰኘ ኮሚቴ በማዋቀር የሱዳንን ግጭት ለማስቆም ውክልና መስጠቱ የሚታወስ ነው።

የመፍትሔ አፈላላጊ የምክክር መድረኩም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ግጭቱን እየመሩ የሚገኙ አካላትን የማደራደርና የሰብዓዊ ድጋፍ የማቀላጠፍ ስራ ትኩረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

በኢጋድ 14ኛው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራቱ ሃገራት ያሉበት የሰላም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የሱዳን ጦር መሪ ጀኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃንንና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ሌፍተናንት ጀነራል ሙሀመድ ሀምዳን ዳጋሎን (ሔሜቲ) በአስር ቀናት ውስጥ ለማነጋገር አቅጣጫ ማስቀመጡም ይታወሳል።

ኢጋድ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተክትሎም ሱዳን ላጋጠማት ወቅታዊ ችግር መፍትሔ ለመስጠትና በቀጣናዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ የአባል አገራት የመሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች አዲስ አበባ ተገኝተው ይወያያሉ።

የኬኒያ ፕሬዝደንት ዶክተር ዊሊያም ሩቶን ተከትሎም የጅቡቲ ፕሬዝደንት እስማዔል ዑመር ጉሌህ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫኪር ማያርዲትን ጨምሮ የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር የተቀሰቀሰው የሱዳን ግጭት ተባብሶ በመቀጠሉ ግጭቱ የበርካታ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ፣ ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀለ ንብረትም እያወደመ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም