ቀጥታ፡

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ጥረት መጠናከር አለበት- የትምህርት ሚኒስቴር 

ድሬደዋ  ሐምሌ 2 / 2015 (ኢዜአ) ፡- የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ  ትውልድ ለመገንባት የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ጥረት  ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ ተናገሩ። 

"ትምህርት ለትውልድ " በሚል የተጀመረው ሀገርአቀፍ የትምህርት ቤቶች ጥራት ማሻሻያ ንቅናቄ በድሬደዋ ተጀምሯል።

ንቅናቄውን ያስጀመሩት ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ እንደገለጹት፤ መንግስት በሀገሪቱ የትምህርት ተደራሽነትን ዕውን ለማድረግ ያስመዘገባቸው ውጤቶችን በትምህርት ጥራት ማረጋገጥ ላይ ለመደገም የተቀናጁ መጠነ ሰፊ  ስራ እያከናወነ ይገኛል ።

በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድ ማፍራት የሚቻለው ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ መሆኑን ተናግረዋል ።

ይህንን ዕውን ለማድረግ በሀገሪቱ ጥናትን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመልክተው፤ የሚፈለገው ለውጥና ውጤት የሚመጣው "ትምህርት ለትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት  ለማካሄድ የተጀመረውን ሀገር አቀፍ ዘመቻ በተቀናጀ መንገድ በመተግበር ይሆናል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ  ካሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ 86 በመቶዎቹ ከደረጃ በታች ናቸው።

የትምህርት ቤቶችን የመሠረተ ልማቶች ለማሻሻል የሚከናወኑ ስራዎች ኢትዮጵያን በአለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ በየደረጃው የሚገኙ  ባለድርሻ አካላት  ዘርፉን በማገዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ  አሻራ ለማስቀመጥ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር  የትምህርት ጥራት መጓደል ለማስተካከል በየደረጃው የሚገኙ ተሰሚነት ያላቸው  የህብረተሰብ ክፍሎች ትብብርና ድጋፍ  ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል ።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ፤  በድሬደዋ ገጠርና ከተማ ከሚገኙ 90 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተፈላጊውን ደረጃ ያሟሉ 2 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ናቸው።  

ይህን ችግር በተቀናጀ መንገድና ርብርብ ለመፍታት  ባለድርሻ አካላት፣ ባለሃብቶችና የዘርፉን አንቀሳቃሾችን በማሳተፍ  በዕውቀት የበለፀገ ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ " ትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄ ማሳካት ለሀገራችን ዕድገትና የብልፅግና ጉዞ መረጋገጥ  ዋና ጉዳይ ነት ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ ናቸው።


 

ከትምህርት ተደራሽነትና ጥራት  ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች ለመፍታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በጥናትና ምርምር የተሰነደውን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ለማድረግ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ፍኖተ ካርታውን ተከትሎ በአዲስ የትምህርት ስርአት የተደገፈና የትምህርት ስብራት የሆነውን የጥራት ጉድለት ፣ የኩረጃና የስነምግባር ችግሮች ለመፍታት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርስቲ መሰጠት መጀመሩ አንዱ ማሳያ መሆኑን አውስተዋል ።

በንቅናቄው ማስጀመሪያ መረሃ ግብር ላይ  በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የዘርፉ አንቀሳቃሾች ፣ ባለሀብቶችና ምሁራን ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ  በሁሉም ዜጎችና ተቋማት ሁለንተናዊ ተሳትፎ በቀጣይ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች  ደረጃ ለማሻሻል በቅርቡ  ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ ማስጀመራቸው በወቅቱ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም