በአማራ ክልል ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል- ክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል- ክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ
ባህር ዳር፣ሃምሌ 2/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት ከሚያበረክቱት ድርሻ አንፃር በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ ።
“ባህላችን ለሰላማችንና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 15ኛው የአማራ ክልል የባህል እና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ዛሬ ተጠናቋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ለአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት ባህልና ኪነ-ጥበብ ከፍተኛ ሚና አላቸው።
የህዝብ መገለጫ የሆኑ የባህልና የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ወደ ጎን ትቶ መልማትም ሆነ ማደግ እንደማይቻል ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግሥት ለባህልና ኪነ-ጥበብ እድገት ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከሚያገለግሉ አስቻይ ሁኔታዎች መካከል ባህላዊ የግጭት አፈታት አንዱ እንደሆነም ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል አሁን ላይ የሚስትዋሉ ችግሮችን ባህላዊ የችግር አፈታት ሥርዓትን በመጠቀም በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በየአካባቢው ባህላዊ ተቋሞች እንዳሉ አውስተው፤ እነዚህ የባህል ተቋማት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተግተው እንዲሰሩም አሳስበዋል።
ኪነ-ጥበብ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገትና ሰላም መስፈን የጎላ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፤ ተተኪ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንዲመጡ መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
በየደረጃው ያለ አመራርም ለባህልና ኪነ-ጥበብ ዘርፉ ዘላቂ እድገት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ዶክተር ይልቃል አመልክተዋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጣሂር ሙሃመድ በበኩላቸው እንደ ሀገርና እንደ ክልል ውስብስብ ችግሮች ቢኖሩም የባህልና ኪነ-ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ እምቅ የኪነ-ጥበብና የባህል ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው፤ ፌስቲቫሉም ይህን አጉልቶ ለማሳየት ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልሉ ህዝብ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ ባህሎችን ጠብቆ በመያዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ እያደረገ ነው ብለዋል።
ከማዕከላዊ ጎንደር የመጣው የምንትዋብ የባህል ቡድን አባል ወጣት ሳሙኤል መስፍን እንዳለው ፌስቲቫሉ የራስን ባህልና የኪነ-ጥበብ ስራ ለሌሎች ከማሳወቅ ባሻገር ከሌሎች ለመማር እድል የሰጠ ነው።
የባህልና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫሉ ሰጥቶ መቀበል የሚያስችል ትልቅ የመማሪያ መድረክ እንደሆነ ጠቅሶ፤ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብሏል።
በመዝጊያው ሥነሥርዓት ላይ የክልሉና የፌደራል የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ከዞኖች የተውጣጡ የባህል ቡድኖች የተገኙ ሲሆን ለክልሉ ባህል መጎልበት የላቀ ሚና ለተወጡ አርቲስቶች እውቅና ተሰጥቷል።