ቀጥታ፡

ወጣቶች በወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የኢትዮጵያን የልማትና የሰላም ተምሳሌትነት ሊያረጋግጡ ይገባል-አቶ ሃዱሽ ስባጋድስ

መቀሌ ሃምሌ 02/2015 (ኢዜአ) የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያ የልማትና የሰላም ተምሳሌት ሆና እንድትታይ የማድረግ አስተዋጾው የጎላ በመሆኑ ወጣቶች በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃዱሽ ስባጋድስ አስገነዘቡ።

ከሀገሪቱ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ዛሬ መቀሌ ከተማ ሲደርሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል ።

በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃዱሽ ስባጋድስ እንዳሉት በኢትዮጵያ ወጣቶች የተጀመረው የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሀገራዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

ሁሉንም ክልሎች በወከሉ ወጣቶች የተጀመረው አገልግሎቱ ኢትዮጵያን የልማትና የሰላም ተምሳሌት የማድረግ አስተዋጾው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቶች ተሳትፏቸውን በማጠናከር አገልገሎቱን የማስቀጠል  ሀላፊነታቸውን  ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

“የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኞች በበኩላቸው ለልማትና ሰላም መረጋገጥ የተጣለብንን ሀላፊነት በአግባቡ በመወጣት የኢትዮጵያ ከፍታ እውን እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን” ብለዋል ።

ከወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኞች መካከል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣው ወጣት ወሰያ ይገበር “በሁሉም ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን አንድነት ወሳኝ በመሆኑ በአንድነትና በፍቅር ለመስራት ዝግጁ ነን” ብሏል።

“ወጣቱ በአገልግሎቱ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በአንድነት ሊተጋ ይገባል” ሲል አመልክቷል።


 

“በልማትና በሰላም ጨምሮ በሁሉም መስክ የዜጎች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ተጋግዘን እውን የማድረግ ዓላማ ይዘን እየሰራን ነው” ያለችው ደግሞ  ከድሬዳዋ አስተዳደር የመጣችው ወጣት ዕሻ ዓብዲ   ናት።

“ለዚህም በሁሉም ክልሎች እየተዘዋወርን ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየሰጠን ነው” ብላለች።

የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹ በነገው እለት በመቀሌና አካባቢው የአቅመ ደካማና የተጎዱ ቤቶችን እድሳት እንደሚያከናውኑ ተመላክቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም