በአፍሪካ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ አገራት ትብብራቸውን ይበልጥ ሊያጠናክሩ ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ አገራት ትብብራቸውን ይበልጥ ሊያጠናክሩ ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 2/2015 (ኢዜአ)፡- በአፍሪካ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ አገራት ትብብራቸውን ይበልጥ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የአፍሪካ የሥራ ጉባኤ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ንግድ ቡድን አመራሮች እና የአፍሪካ የሥራ ዘርፍ አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጉባኤው በአፍሪካ የሥራ ፈጠራን ለማሳካት አህጉራዊ ትስስር ለማጠናከር መሠረት የጣለ ነው።
በአፍሪካ ሰፊ ስራ አጥነት ችግር መኖሩን በመገንዘብ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ያለውን በርካታ የወጣቶች ቁጥር እንደ መልካም ዕድል በመውሰድ ሁሉም ሀገራት ለለውጥና ለብልፅግና ሊጠቀሙበት እንደሚገባም አንስተዋል።
የወጣቶችና የሴቶች ስራ አጥነት በአህጉሪቱ ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት ይህን ችግር ለመሻገር አህጉራዊ ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ የሥራ ፈጠራን ማስፋፋት፣ ሥራ አጥነትን መቀነስ የአህጉሪቱ መንግሥታት ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል።
ለዚህ ደግሞ በአህጉሪቱ ያለውን ሀብት በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ወጣቶችንና ሴቶችን ሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ማድረግ በ2063 የበለፀገች አህጉር ለመፍጠር የተያዘውን ግብ እንደሚያሳካም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትና የሥራ ፈጠራ አድማስን ለማስፋት በትኩረት እየሠራች መሆኑ ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በዚህም በየዓመቱ በአማካኝ ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ማስቀመጧን ተናግረዋል።
በቀጣይም ከአፍሪካ ህብረት እና አፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ንግድ ጋር በመተባበር በአፍሪካ የስራ ዕድል ፈጠራ አቅም እንዲጎለብት የበኩሏን ሚና ትወጣለች ነው ያሉት፡፡