ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሥራ ፈጠራን ከማሳደግ ባሻገር ጠንካራ የሥራ ባህል መገንባት ይገባል- የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሥራ ፈጠራን ከማሳደግ ባሻገር ጠንካራ የሥራ ባህል መገንባት ይገባል ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ የሥራ ጉባዔ "ሥራ አጥነት፣ የሥራ ባህል እና የሥራ ዕድል ፈጠራ" በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት በኢትዮጵያ በስራ ዕድል ፈጠራው መስክ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ አመለካከት እውቀትና ክህሎት ላይ መስራት ይገባል። 

በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጠንካራ የሥራ ባህልን ማዳበር ይገባል ነው ያሉት። 

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ የሥራ ዕድል መኖሩን ገልጸው፤ ይህንን በአግባቡ ለመጠቀም እውቀት ክህሎትና አመለካከት ላይ በስፋት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዓለምአቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል። 

መንግሥት ዘላቂ፣ ጥራት ያለው እና ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን በማንሳት፤ የግሉ ዘርፍም ሀገርን ለማሻገር በሥራ ፈጠራና በሥራ ባህል ለውጥ ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። 

እንደ ሀገር ሰፊ የሥራ ዕድል ቢኖርም በርካታ ሥራ አጥ ወጣት ያለባት ሀገር በመሆኗ ይህንን ለመቀየር የሥራ ፈጠራን የማስፋትና ጠንካራ የሥራ ባህል መገንባት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። 

የኢትዮጵያን የእድገት ትልም ለማሳካት አምራቹን የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም እና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ጠቅሰዋል። 

መንግሥት የውጭ የሥራ ሥምሪት ላይም ብቁ ወጣቶችን በዓለም ገበያ ለማሰማራት ትኩረት ማደረጉን ተናግረዋል። 

በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት በየአካባቢው ያሉ አቅሞችን መሠረት ባደረገ መልኩ የሰው ኃይል የሚያፈሩበትን ምደባ ለማድረግ ጥናት መደረጉንም ገልጸዋል። 

ይህም ተቋማቱ በትኩረት መስክና በልማት ኮሪደር እንዲደራጁ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓትን ወድ ስራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም