ቀጥታ፡

ምክክርና መደማመጥ - የኢትዮጵያ ቀለም

 

                           ምክክርና መደማመጥ - የኢትዮጵያ ቀለም

                             በቀደሰ ተክሌ

ምክክር ከቀደምት ኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ ህይወት ውስጥ የተሰናኘ የጋራ ሀብትና ሀገራዊ ጥበብ ነው። ቀጠሮ ይዞ ተቀምጦ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ተመካክሮ መግባባትም የኢትዮጵያ አንዱ ቀለም ነው። ችግር ሲያጋጥም ብቻ ሳይሆን መልካም የሆኑ ክዋኔዎችን እንኳ ለመተግበር አስቀድሞ መመካከር በብዙዎቻችን ዘንድ  ያለና የነበረ ነው- አሁን እየሳሳ ቢመጣም ። መመካከር ሀሳብን በመለዋወጥ የሚበጀውን የጋራ የማድረግ ጥበብ ነው። ነጠላ ሀሳብ በውይይት ጎልብቶ ጠንካራ ይሆናል። በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚደረግ ማንኛውም ውይይት ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በንግግር ሂደት ውስጥ መደማመጥ ሲኖር ብቻ ነው።

ሀሳብን ጆሮ ሰጥቶ በማድመጥ ከተረዱ በኋላ የራስን እይታ በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ ጎን መስጠት የትልቅነት ማሳያ ነው። ፍሬያማ ውይይት ሊደረግ የሚችለውም በዚህ መንገድ ከሄደ ብቻ መሆኑ አያጠራጥርም። በተቃራኒው "የኔን ብቻ ስሙልኝ" በሚል ቀጭን መስመር ላይ ቆሞ ለውይይት መቅረብ፤ አስፈጽሙልኝ ነው እንጂ እንምከርበት ከሚል ጽንሰ ሀሳብ የራቀ ይሆናል። በዓለማችን በተለይ አሁን አሁን ሀገራችንንም ጭምር እያስጨነቀ ያለው በራስ እይታ ብቻ በተቃኘችና ከመርፌ ክር የቀጨጨች የሀሳብ ድልድይ ላይ መቆም ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ በግራና በቀኝ የሚመጡ ሌሎች እይታዎችን ለማስተናገድ በመቸገር የመውደቅና መጣል ስሜት ውስጥ ያስገባል።

የሀገራችን ብሂል "ድር ቢያብር" ሆኖ ሳለ "ያለ እኔ ማን" በሚል የተዛባ ግንዛቤ አቅማችንን የማዳከም ቀውስ ውስጥ ለመግባት የዳዳንበት ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎችን እንደ ሀገር እያየን ነው። "የኔን ቁስል እንጂ የሌላውን ሞት አላይም" ማለት የከፋ ራስ ወዳድነት ነው። ስለዚህ በመደማመጥ የራስን ጉዳት በማስረዳት የወንድምን መከፋት ሰምቶ ሚዛናዊ እይታ ላይ መቆም የሚያስፈልግበት ምዕራፍ ውስጥ መግባት የግድ ይሆናል።

እንደ ሀገር የገጠሙንን ስብራቶች ለማከም በሀገር ልጅ ሀገር በቀል መፍትሄ በሚል የምክክር ሀሳብ ተይዞ ሂደቱን እየተመለከትን ተስፋንም አንግበን በመጠባበቅ ላይ ነን። በሚቀጥለው ዓመት መካሄድ የሚጀምረው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ሂደት የተግባቦት ውጤትን ያመጣ ዘንድ ለመደማመጥ ቅድሚያ ሰጥቶ ለውይይት መቀመጥን ይጠይቃል። ያለመደማመጥ መዘዝ ግጭትን እንደሚያስከትል አበው በብሂላቸው "ያልሰማ ጆሮ ከጎረቤት ያጣላል" በማለት ገልጸዋል። ዛሬ በስማ በለው እና በሬ ወለድ ሀሳብ ደም ለመፋሰስ የሚዳዳ ትውልድ እያፈራን መሆኑ የሚሸሸግ አይደለም።

አስተያየታቸውን የሰጡን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኮንታ ወረዳ ቤተክህነት ሥር አገልጋይ ካህን የሆኑት ቄስ ቤዛ ጥላሁን በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ስለሌላ ሰው ብሎ ራስን በትህትና ዝቅ ማድረግ የከፍታ መንገድ የትልቅነት ማሳያ መሆኑ ተጠቅሶ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከፍ ከፍ ለማለት የሚፈልግ ራሱን ዝቅ ማድረግ ይገባል የሚሉት ቄስ ቤዛ፤ ይህ ደግሞ ለታይታ ሳይሆን በፍጹም ከልብ ከሆነ ትህትናና ቀናነት ከሆነ ከፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ከማህበረሰቡም ጭምር ያገኛል ባይ ናቸው። በመሆኑም በሁለትዮሽ ግንኙነት ውስጥ መመካከርን ትቶ "የኔ ብቻ የተሻለ ነው" ወይም "የኔን ብቻ ተቀበል" ማለት ፍላጎትን በሀይል መጫንን በማምጣት ልዩነት እንድሰፋ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ መቀባበሉ ልጎላ እንደሚገባ መክረዋል። እንዲህ ሳይሆን ቀርቶ በልበ ክፉነት ሌላው ላይ ፍላጎትን ለመጫን የሚፈልግ ካለ ድምር ውጤቱ ከፈጣሪ ዘንድ የሚከፈል በመሆኑ በጊዜ ሂደት ማወራረዱ የማይቀር በመሆኑ መቆጠብ ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል ። ስለሆነም በማንኛውም ጉዳይ የሌላውን ሁኔታ ተመልክቶ የሚስተካከል ከሆነ ማገዝ እንጂ የማይረባ አድርጎ በመቁጠር ማንቋሸሽ በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ አለመግባባትን የሚያስከትል ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ከምንም በላይ በሰው ልጆች መካከል መግባባትን ከሚፈጥሩ ሰብአዊ እሴቶች መካከል አንዱ ትህትና መሆኑን ተረድቶ መጠቀም ይገባል። በትህትና የተሞሉ አንደበቶች የማያሸንፉት ሀሳብ አይኖርም። የተናደደውን የማስታገስ፤ የጠነከረውን የማለዘብ አቅም በትህትና ለተሞሉ ቃላት ተችሯል ነው ያሉት።  በሀገር ግንባታና የሰላም ማስፈን ሥራ ውስጥ ከራስ ጥቅም ይልቅ የሌላን ሰው ህልውናና ሥነ ልቦና መጠበቅ ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግም እንዲሁ። 

ሀገራዊ የምክክር ሂደት በዚሁ መንገድ ችግሮችን ይፈታል የሚል ተስፋ በመያዝ አብሮ ለመስራት ጥረት እያደረጉ እንዳለ ገልጸዋል። ውይይቱ ሲጀመር "የኔ ብቻ ይደመጥ" የሚል አይነት አስተሳሰብ ፈጽሞ ወደ ውይይት መድረክ መቅረብ እንደሌለበትም በአጽንኦት አስገንዝበዋል።

የእሳቤ ሚዛን ለመጠበቅ ለሰው ልጅ በእኩል ደረጃ መመካከር ትልቅ ትርጉም እንዳለው የሚገልጹት ደግሞ በሸካ ዞን የየኪ ወረዳ እስልምና ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ፋሪስ ሙሳ ናቸው። እንደ ሀገር አሸናፊ እና ተሸናፊ የሚል ነገር ሊቀር ይገባል ይላሉ። ሁሉም በወንድማማችነት መንፈስ ችግሮቹን ተመካክሮ መፍታት ነው ያለበት የሚል አቋም እንዳለቸው ተናግረዋል። ሀገራዊ የምክክር ሂደት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የላላው የመመካከር ባህላችን የሚጎለብትበት እና ለሀገራዊ ችግሮቻችን ሀገራዊ ምላሽ የምንሰጥበት የሀገር ሀብታችን ነው ብለዋል። ይህ ምክክር በተወሰኑ አካላት ብቻ የሚታጠር ሳይሆን ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ በተወካዩ በኩል የሚያሳትፍ መሆኑ ትልቅ ሀገራዊ ለውጥ ለማስመዝገብ የያዘውን ዓለማ ከግብ የሚያደርስ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን በኢትዮጵያችን ሰላምና ልማት ላይ እንቅፋት እየሆነ ያለውን ያለመግባባት ችግር ለመፍታት ጠመንጃ ሳይሆን የምክክርን ትጥቅ ማንገብ ትክክለኛ የመፍትሄ አማራጭ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢዜማ ፓርቲ የዳውሮ ዞን ተወካይና የዞኑ ፖለትካ ፓርቲዎች ሰብሳቢ አቶ አጥናፉ በታሮ ናቸው። የምክክር ትጥቃችን በአግባቡ ውጤት እንዲያስመዘግብ "የኔ ሀሳብ የእሱ፤ የእሱ የኔ ነው" በማለት የሚበጀውን የጋራ ማድረግ ያስፈልጋል። በምክክር ሂደቱ የማያስማማ ሀሳብ ቢኖር እንኳ ተነጋግሮ መተማመን ወይም በሀሳብ ደረጃ ተደማምጦ መስማማትን መሠረት ያደረገ ውይይት ለማካሄድ ራስን አዘጋጅቶ መቅረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በሀገራዊ ምክክሩ "ስክነት፣ ብልሃትና ማስተዋል" የታከለበት እሳቤን ይዞ መንቀሳቀስ ከተቻለ ለሀገር የሚበጅ የችግሮቻችን መፍትሄ ቶሎ  እንደሚገኝ አንስተዋል። ሁላችንም የኢትዮጵያን ሰላምና የጋራ ልማት በማሰብ ከግል ጉዳይና የግል ስሜት በተለየ መንገድ መመካከር አለብን የሚል አቋማቸውን አጋርተዋል። በተለይ የትላንት አጀንዳ ትቶ የነገን መልካም ነገር ከግምት ውስጥ ያስገባ አዳዲስ ሀሳቦች የሚንጸባረቅበት የወንድማማችነት ንግግር በየመድረኮች ሊደመጥ ይገባል የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

ሀገራዊ የምክክር ሂደት በአሁን ሰዓት በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን በመስራት ላይ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ እየታየ ያለው የህዝብ ተሳትፎ የሚደነቅ ነው። ትልቅ ተስፋ ከፊቱ ይነበባል። ነገ የተሻለች ኢትዮጵያን እናያለን በሚል እምነት ሥራው ቶሎ እንዲጀመር እየገፋፋም ይገኛል። በዛውም ጫንቃው ላይ የተሸከመው የ"ተበድያለሁ" ሸክሙን ለማራገፍ የቸኮለ ይመስላል። ታዲያ የምክክር ሂደቱ ሲጀመር ስክነት እና ትህትና ፈጽሞ ሊዘነጉ አይገባም።

የኔን ሀሳብና ችግር ሳስደምጥና እንዲቀረፍልኝ ስፈልግ ሌላውን ጎድቶ መሆን የለበትም። ያ ከሆነ ችግርን ከአንዱ ወደ አንዱ ማንከባለል እንጂ ተወያይቶ መፍታት ለሚል ቋንቋ አይስማም። በመሆኑም ማድመጥን ማስቀደም ሚዛናዊ ማገናዘብን ያመጣልና ሊሰመርበት ይገባል። 

ሰላም!

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም