ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንግስት ባደረገልን መልካም አቀባበል ከችግርና ሞት ታድጎናል---ሱዳናዊያን ስደተኞች

መተማ ሐምሌ 2/2015 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ መንግስት ድንበሩን ክፍቶ አድርጎ ባደረገልን መልካም አቀባበል ከችግርና ከሞት ታድጎናል" ሲሉ በሱዳን ግጭት ተሰደው  በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የተጠለሉ ሱዳናዊያን ስደተኞች ገለጹ።

ስደተኞቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በኢትዮጵያ የተደረገላቸው አቀባበልና ድጋፍ በስደት ወቅት ሊደርስባቸው ከሚችል እንግልትና ስቃይ ታድጓቸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት አብዱልከሪም ሙሃመድ እንዳለው በሱዳን በተከሰተ ግጭት ምክንያት ከአገሩ ተሰዶ ላለፉት ሦስት ወራት በመተማ ዮሐንስ መጠለያ ጣቢያ እያሳለፈ ይገኛል።

እሱን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች ወደ መተማ ሲገቡ በኢትዮጵያ መንግስት መልካም አቀባበልና ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቅሶ ለእዚህም ያለውን ምስጋና ገልጿል። 

ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ቀን ጀምሮ ምግብ፣ የመጠጥ ውሃና መጠለያ እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ አንዳንዴ የሚስተዋለው የምግብና የመድሀኒት እጥረት እንዲስተካከል ጠይቋል። 

"ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ትልቅ አክብሮትና ምስጋና አለኝ" ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ ሱዳናዊ ተፈናቃይ አሚራ ሙሃመድ ናቸው።

ኢትዮጵያ ድንበሯን ለስደተኞች ክፍት አድርጋ መቀበሏ በተለይ በስደት ወቅት በሴቶችና ህጻናት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ችግርና ሞት ማስቀረቱን ተናግረዋል።


 

በሱዳን በተፈጠረ ግጭት ከ13 የቤተሰብ አባላት ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ገልጸው፣ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በፍቅር እንደተቀበሏቸው ተናግረዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ በመጠለያው በቆዩባቸው ጊዜያት የምግብና የውሃ ድጋፍ እያገኙ ቢሆንም ለህጻናት ልዩ እንክብካቤ በማድረግ በኩል የተወሰኑ ክፍተቶች አሉ።

በተለይ ለህጻናት የሚሆን የአልሚ ምግብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የጠየቁት ተፈናቃዩዋ፣ "በአካባቢው ስደተኞች በነጻነት መንቀሳቀስ የምንችልበት ሁኔታ ሊመቻችልን ይገባል" ብለዋል።  

ሌላኛው ስደተኛ አቶ አብዱላዚዝ ሀሰን በበኩላቸው እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ያደረጉልን አቀባበል የባዕድነት ስሜት እንዳይሰማን አድርጓል።

"በስደት መጥተን የተደረገልን ወንድማዊ አቀባበል በአገሬ ያለው ያህል እንዲሰማኝ አድርጓል፤ ለእዚህም ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው" ያሉት አቶ አብዱላዚዝ፣ በመተማ መጠለያ ጣቢያ ምግብ፣ ውሃና ማረፊያ ከማቅረብ ጀምሮ የጤና ምርመራ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።


 

በመጠለያው በኢትዮጵያ መንግስትና በተለያዩ ለጋሽ አካላት የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ በምግብ አቅርቦት በኩልም የለመድነው ምግብ ቢሆን ሲሉ ጠይቀዋል።    

በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የመተማና አካባቢው የስደተኞች ካምፕ አስተባባሪ አቶ ታምራት ደምሴ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በሱዳን በተከሰተው ግጭት ከስምንት በላይ ሀገራት ዜጎች በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። 

ስደተኞቹ የምግብ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የጤናና መሰል አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይ ከተባበሩት መንግስታትና ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመሆን የስደተኞችን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት እንደሚሰራም ገልጸዋል።


 

አቶ ታምራት እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገሮች ተሰደው የመጡ ተፈናቀዮች በመጠለያ ካምፖች ይገኛሉ። 

በመተማና አካባቢውም እስካሁን ድረስ የተጠለሉ ስደተኞች ከ15 ሺህ በላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። 

የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ በኩል ኢትዮጵያ ለሌሎች ትምህርት የሚሆን የቆየ ልምድ እንዳላት ያስታወሱት አስተባባሪው፣ በችግር ውስጥም ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኗን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም