ቀጥታ፡

የሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪትን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው-የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሐምሌ 1/2015(ኢዜአ)፡- የሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪትን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ በሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ ከሆኑ ተቋማት አንዱ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።

በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና የውጭ አገር የሥራ ስምሪት የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውን ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል።

በቀጣይም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት በመስጠት የሚሰራ መሆኑን በመግለጽ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤ በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ችግሮች እየተፈተነችም ቢሆን በሥራ ዕድል ፈጠራ ስኬቶችን አስመዝግባለች ብለዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራው በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ትብብር የመጣ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፤ በበጀት ዓመቱ ለ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

የውጭ አገራት የሥራ ስምሪት በቴክኖሎጂ ታግዞ የገበያ መዳረሻዎችን ጥናት ባደረገ እና የትኛው ሙያ በየትኛው ሀገር እንደሚፈለግ በመለየት ማሰማራት ተችሏል ብለዋል።

በውጭ አገራት የሥራ ስምሪት 100 ሺህ ዜጎችን መብታቸውን፣ ጥቅምና ክብራቸውን ባስጠበቀ መልኩ መቀጠራቸውን ገልፀዋል።

የውጭ ሃገር የስራ ስምሪቱን ዲጂታላይዝድ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ የሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪቱንም ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም