ቀጥታ፡

የእንስሳት ዝርያ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው- የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ሐምሌ 01/2015(ኢዜአ)፡-  የእንስሳት ልማት ኢኒስቲትዩት የእንስሳት ዝርያ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም በዘርፉ ምርት እምብዛም ተጠቃሚ አለመሆኗን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አሁን ላይ መንግሥት የእንስሳት ሀብትን ከሌሎች የውጭ ንግድ መስኮች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ሲሆን ከስራዎቹ መካከል በምርትና ተጠቃሚነትም የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ይጠቀሳል።

የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሳህሉ ሙሉ ኢትዮጵያ በእንስሳት ኃብቷ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የዝርያ ማሻሻል ስራዎች በተቋሙ እየተከናወኑ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የእንስሳቱን ዝርያ ከማሻሻል ባለፈ የእንስሳት ተዋጽኦ  ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እና ምርታማነታቸው እንዲያድግ እየሰራ ነው ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ልማትም የእንስሳት መኖን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር የእንስሳት ሀብት ልማት በተለይም  የወተት ላሞችን ዝርያ የማሻሻል ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት ዶክተር ሳህሉ።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም