የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ለዓለም ለማስተዋወቅ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ላይ በትብብር መስራት ይገባል-የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ለዓለም ለማስተዋወቅ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ላይ በትብብር መስራት ይገባል-የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ
አዲስ አበባ ሐምሌ 1/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ለዓለም ለማስተዋወቅ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ላይ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።
ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ቀርጸው እየሰሩ ካሉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ በቀዳሚነት እንደምትጠቀስ አቶ ኃይለማርያም ለኢዜአ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በደን ልማት፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ የተሳካ ስራ መስራቷን አንስተዋል።
በእርከን ስራ እና የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ከፍ ያለ ስም ማትረፏን ጠቅሰው በአረንጓዴ አሻራ ልማት የጀመረችው ጥረትም አስደናቂ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ለዓለም ለማስተዋወቅ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ላይ በትብብር መስራት እንደሚገባ ነው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ያመለከቱት።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ከራስ አልፎ የአካባቢውን አገራት ተጠቃሚነትም ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለቀጣናዊ የልማት ትስስር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ልማት መርሐ-ግብር 25 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል እቅድ ይዛ በመስራት ላይ ትገኛለች።