ቀጥታ፡

በውጭ የሚኖሩ ወገኖችን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የሚያሳትፍ የፖሊሲ ሰነድ እየተዘጋጀ ነው-አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ሐምሌ 1/2015 (ኢዜአ)፦ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በሰው ሰራሽ አስተውሎት /አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ/ ቴክኖሎጂ የሚያሳትፍ የፖሊሲ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያን እስከ 2022 ዓ.ም የአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የፖሊሲ፣ የመሰረተ-ልማት ግንባታና ሥነ-ምህዳር የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

በዚሁ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ግርማ፤ ኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓተ-ምህዳር መገንባት በሚያስችል ሂደት ላይ መሆኗን ገልፀዋል፡፡

በዚህም የዘርፉን መሠረተ-ልማትና ሥነ-ምህዳር በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችልና በውጭ የሚኖሩ ወገኖችን የሚያሳትፍ የፖሊሲ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በዘርፉ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለመሆን ተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰው፤ መንግሥት ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ መልስ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸቱን ገልፀዋል።

በመሆኑም በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትልውደ-ኢትዮጵያውያን በዘርፉ የመሳተፍ ዕድል መፈጠሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉ ልምድ ያላቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ ተቋማት ጭምር የሚሰሩ በርካታ ዜጎች ስላሉ ለዘርፉ እድገት የላቀ አበርክቶ እንደሚኖራቸውም ገልፀዋል፡፡

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚነት የሚያጎላና ደኅንነቱን ማስጠበቅ የሚያስችል አሠራር የሚከተል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አስተባባሪ ዶክተር በአካል ግዛቸው፤ ኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረት ያላት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሰደሩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርምሮችና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶች ለዘርፉ መሠረት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ በተበጣጠሰ መንገድ ቢኖርም በሕግና በሥርዓት የተመራበት ጊዜ አልነበረም ያሉት ዶክተር በአካል፤ ወጥ የሆነ አሠራር ሊበጅለት ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከፖሊሲው ቀጥሎ የሚወጡ ስትራቴጂዎችና አዋጆች በሀገር ደኅንነት ላይ አደጋ እንዳይፈጥሩ የቁጥጥር ሥርዓት ሊዘጋጅላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም