ቀጥታ፡

በእሳት አደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ ይደርጋል-ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ

ጅግጅጋ ሐምሌ 1/2015(ኢዜአ):- በእሳት አደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ገለጹ።

ርዕሰ-መስተዳድሩ እና የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በጅግጅጋ ትናንት ሌሊት ታይዋን ተብሎ በሚጠራው የገበያ ስፍራ የተከሰተው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ያደረሰውን ጉዳት ተመልክተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በከተማው ትልቁ የገበያ ማዕከል እና የበርካታ ቤተሰቦች መተዳደሪያ በነበረው ስፍራ በደረሰው አደጋ ማዘናቸውን ገልጸዋል።


 

በአደጋው ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን መልሶ ለማቋቋም ከሕብረተሰቡ ጋር በትብብር እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር አሊ አብዲ የእሳት አደጋው ከአንድ የልብስ መሸጫ ሱቅ መነሳቱን ገልጸው በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ተናግረዋል።

የከተማው የእሳት አደጋ መከላከያ ግብረ ኃይል፣ የሐረሪ ክልል እሳት አደጋ መከላከያ ቡድን የሶማሌ ላንድ ሀርጌሳ ከተማ እሳት አደጋ መከላከያ እና የከተማው ነዋሪዎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ እሳቱን መቆጣጠር መቻሉንም አመልክተዋል።

የእሳት አደጋውን መንስኤ ፖሊስ እያጣራ እንደሚገኝም ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም