ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ ሐምሌ 1 /2015 (ኢዜአ)፦ የ2015 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል።

መስከረም 20 ቀን 2015 ወልቂጤ ከተማ ከአርባ ምንጭ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ አንድ ብሎ በጀመረው የውድድር ዓመት እስከ አሁን 239 ጨዋታዎች ተደርገዋል።

የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ድሬዳዋ ከተማ በ39 ነጥብ 10ኛ ሲሆን አስቀድሞ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ 63 ነጥብ ይዞ የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል።

ድሬዳዋ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት ገጥሞታል።

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ 16ኛ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫውን ያነሳል።

የኮከብ ግብ አግቢ፣የኮከብ ተጫዋች፣የኮከብ ተስፈኛ ተጫዋች፣ የኮከብ ግብ ጠባቂ እና ሌሎች ሽልማቶችም ይበረከታሉ።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ቶጎዋዊ አጥቂ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በ25 ግቦች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል።

ለኮከብ ተጫዋች፣ኮከብ ተስፈኛ ተጫዋች እና ኮከብ ግብ ጠባቂ እጩዎች የድምጽ አሰጣጥ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የቴሌግራም ገጽ ከሰኔ 26 እስከ 29 2015 ሲካሄድ ቆይቷል።

ቶጎዋዊው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ እና ቢኒያም በላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ያሬድ ባየህ፣አለልኝ አዘነ እና ፉአድ ፈረጃ ከባህር ዳር ከተማ፣የወልቂጤ ከተማው ጌታነህ ከበደ እና የኢትዮጵያ መድኑ ባሲሩ ኡመር የኮከብ ተጫዋቾች እጩ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።

ዘላለም አባተ እና አበባየሁ አጂሶ ከወላይታ ድቻ፣አማኑኤል ተርፉ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ዮሴፍ ታረቀኝ ከአዳማ ከተማ የዓመቱ ኮከብ ተስፈኛ ተጫዋች እጩ ውስጥ የተካተቱ ተጫዋቾች ናቸው።

በዓመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ አቡበከር ኑራ ከኢትዮጵያ መድን፣ፔፔ ሰይዶ ከሀዲያ ሆሳዕና እና ቢኒያም ገነቱ ከወላይታ ድቻ ተካተዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም