የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማብራሪያ በመገናኛ ብዙኃን እይታ - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማብራሪያ በመገናኛ ብዙኃን እይታ
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2016 በጀት ዓመት የተዘጋጀውን 801 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀትን በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
ከዛ ቀደም ብሎ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለምክር ቤቱ አባላት የመንግሥታቸውን የ2015 ዓመት የሥራ አፈፃጸምና የኢትዮጵያን አሁናዊ የሰላምና የጸጥታ፣ የኢኮኖሚና የውጭ ግንኙነት እንዲሁም ሌሎች በርካታ አገራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በአገር ውስጥና በውጭ የመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ማግኘት ችሏል። ከፈረንሣዩ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አንስቶ እስከ የቱርኩ ቲ.አር.ቲ ዎርልድ (TRT World) ፣ እስከ የተባበሩት ዓረብ ኢማራቶች አል-ዐይን፣ ከቢቢሲ እስከ የአሜሪካ ድምጽ፣ ከጀርመኑ ዶቼ ቬሌ እስከ ኦል አፍሪካ ደግሞ ማብራሪያውን ሽፋን ሰጥተውታል።
ሰላምን በሚመለከት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች "በመሬት ምክንያት መባላት፤ መገዳደል አያስፈልግም። መሬት የጸብ ምንጭ መሆን የለበትም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ሕዝቦች ተወያይተው፣ ተመካክረው አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሳይሆን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ጊዜ ወስደው በሰከነ መንገድ የትኛው ክልል መኖር እንደሚፈልጉ መወሰን ይችላሉ" በማለት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት እንዳለው ማንሳታቸውን የመገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) ይዞት በወጣው ዘገባ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመከላከያና ከሌሎች መደበኛ የጸጥታ ኃይሎች ውጭ የታጠቀ ኃይል እንደማይኖር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መናገራቸውን ገልጿል።
የጀርመን ድምጽ በበኩሉ የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በይገባኛል የሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ጉዳይ "በሰከነ መንገድ" ሊታይ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል ሲል በዘገባው አመላክቷል።
ላለፉት 30 ዓመታት በሁለቱ ክልሎች "የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች" መኖራቸውን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን የአማራ እና የትግራይ ሕዝቦች "በሰከነ መንገድ እንዲያዩ" መክረዋል፤ ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ ግን ጠቃሚ አለመሆኑን መናገራቸውን አስነብቧል።
በትግራይ የነበረው ጦርነት የተቋጨበትን የፕሪቶሪያ ስምምነት ለመተግበር መንግሥታቸው የሄደበትን ርቀት ባብራሩበት ምላሻቸውም "ባለፈው ስድስት ወር ለሰላሙ የሄድነው ርቀት እጅግ በጣም ብዙ ነው" ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የመልሶ ግንባታን የተመለከቱ በርካታ ውዝፍ ሥራዎች በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች እንዳሉ በማውሳት "የገነባንው ትምህርት ቤትም ገና ነው ሙሉ አይደለም፤ መብራቱም ገና ነው፤ ስልኩም ገና ነው፤ ሥራ ይፈልጋል" ማለታቸውን የጀርመን ድምጽ በዘገባው አመልክቷል።
ቢቢሲ አማርኛ ሰፊ ሽፋን በሰጠው ዘገባው “በተከበረው ምክር ቤት ፊት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በኩራት እና በእምነት የምገልጸው፣ ከዚህ ምስኪን ሕዝብ አንድ ብር አንሰርቅም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መናገራቸውን አስነብቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በእሳቸው አነሳሽነት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ኦዲት እንዲደረግ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንደሆነም ቢቢሲ አስፍሯልነው።
በተመሳሳይ የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በዘገባቸው ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል።
የኢትዮጵያ የብድር ዕዳ ከኢትዮጵያ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚይዘው ምጣኔ ወደ 38 በመቶ ዝቅ ብሏል መባሉን የተለየ ትኩረት ሰጥተው የዘገቡት ሆኗል።