የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ለመሳተፍ ከወዲሁ ፍላጎታቸውን እያሳዩ ነው- የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ለመሳተፍ ከወዲሁ ፍላጎታቸውን እያሳዩ ነው- የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2015 (ኢዜአ)፦የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በ2016 በጀት ዓመት በሚጀመረው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ውስጥ ለመሳተፍ ከወዲሁ ፍላጎታቸውን እያሳዩ መሆኑን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን አስታወቀ።
የካፒታል ገበያ ባለሃብቶች፣ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች ወይም መንግስት ለሚያስፈልጋቸዉ ኢንቨስትመንት ካፒታል በጥሬ ገንዘብ አሊያም በአይነት የሚያሰባስቡበትና የሚያገኙበት ገበያ ነዉ፡፡
ይህም ካፒታል በማሰባሰብ፣ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዲዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ እና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ልማት ያግዛል፡፡
በተጨማሪም በቀላሉ ቢዝነስ ለመጀመር፣ ለማስፋፋት እና የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎችን በአፋጣኝ ለማግኘት እንዲሁም የዉጭ ኢንቨስተሮችን በቀላሉ ለመሳብና ከትናንሽ ቢዝነሶች እስከ ትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ለመመስረት እድል ይፈጥራል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ትናንት ለሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፤በቀጣይ ዓመት የሚጀመረው የካፒታል ገበያ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ሚናው የጎላ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በተለይም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሆነው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ሰፊ እድል እንደሚፈጥር ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ሰለሞን ዘውዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የካፒታል ገበያን በሚመለከት በአገር ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡
በዚህም በኀብረተሰቡ ዘንድ በዘርፉ የመሳተፍ ፍላጎት መጨመሩን ነው የገለጹት፡፡
ከአገር ውስጥ በተጨማሪ የውጭ ኩባንያዎች ከወዲሁ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በቅርቡ ኬንያ የሚገኝ አንድ ባንክ በዘርፉ ለመሳተፍ ያለውን ፍላጎት መግለጹን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ለሚጀመረው የካፒታል ገበያ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በውጭ አገራት ከሚገኙ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በዘርፉ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አካላትን በመለየት የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
የካፒታል ገበያው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመትና ቁጠባን ከማሳደጉ ባሻገር የዲጅታል ግብይትን በማፋጠን በኩል ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ነው ያረጋገጡት ።
ይህም አዳዲስ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት፡፡
በቀጣይም በመላ አገሪቱ የካፒታል ገበያውን ተደራሽ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን እንደሚከናውኑም ጠቁመዋል።