በአፍሪካ አገራት መካከል የዲጂታል ሴክተር ትብብርን በማጠናከር ዘርፉ ለስራ እድል ፈጠራ ያለውን አቅም መጠቀም ይገባል-የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ አገራት መካከል የዲጂታል ሴክተር ትብብርን በማጠናከር ዘርፉ ለስራ እድል ፈጠራ ያለውን አቅም መጠቀም ይገባል-የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2015(ኢዜአ) በአፍሪካ አገራት መካከል የዲጂታል ሴክተር ትብብርን በማጠናከር ዘርፉ ለስራ እድል ፈጠራ ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
ሚኒስትሯ ይህን ያሉት በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የስራ እድል ፈጠራ ፎረም ላይ ነው።
በዚህም ኢትዮጵያ የገበያ ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን በመደገፍ አዳዲስ የስራ እድሎች እንዲስፋፉ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የስራ እድል ፈጠራ የአፍሪካ ዋነኛው አጀንዳ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ በተለይ በአፍሪካ አገራት መካከል የዲጂታል ሴክተር ትብብርን በማጠናከር ዘርፉ ለስራ እድል ፈጠራ ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የዲጂታል ዘርፉ አዳዲስ የንግድና የሥራ እድሎችን መፍጠር ረገድ እድል ይዞ መምጣቱንም አብራርተዋል፡፡
በኢኮኖሚ ትብብር ቀጣናዊ ውህደትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እውን ለማድረግም በክህሎትና እውቀት ላይ መዋለንዋይ ማፍሰስ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በክህሎትና ሙያ ዘርፎች በቂ ስልጠና በመስጠት ወጣቶችን ማብቃት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡