ደም በመለገስ ህይወት የማዳን ወገናዊ አለኝታነት 

 ደም በመለገስ ህይወት የማዳን ወገናዊ አለኝታነት 

ደም የመለገስ ውሳኔ ሰዎችን ከሞት  የመታደግ ተግባር ሲሆን ፤ ይህን ለማድረግ  ሀብታም ወይም ድሀ መሆንን አይጠይቅም።

ጤነኛ መሆኑ በህክምና የተረጋገጠና ዕድሜው ከ18 እስከ 65 ዓመት የሆነው ሰው ሁሉ ሊፈጽመው ይችላል፤ ሰዎች በድንገተኛ አደጋ ወይም በህመም ምክንያት ተጨማሪ ደም ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

 በተለይ አንዳንድ እናቶች በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድና በድህረ ወሊድ ጊዜ ደም የሚያስፈልጋቸው ጊዜ በርካታ ነው።

 የእነዚህን ወገኖች ህይወታቸውን ከስቃይ ወይም ከሞት መታደግ የሚቻለው ደግሞ በጎ ፈቃደኞች በሚለግሱት ደም ነው።

በአለም ላይ ይህን በቅጡ የተገነዘቡ በርካታ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነብሶችን ከሞትና ከህመም እየታደጉ ይገኛሉ።

በአንድ አገር የደም ፍላጎት የተሟላ ነው የሚባለውም ቢያንስ ከሀገሪቱ ሕዝብ ከአንድ እስከ ሁለት በመቶው የሚሆነው በመደበኛነት ደም ሲለግስ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የደም መለገስ ባሕል በሚፈለገው ደረጃ አላደገም፤ በዚህም ምክንያት በርካቶች መዳን እየቻሉ በአሳዛኝ ሁኔታ ለህልፈት ሲዳረጉ ይስተዋላል።

ሰው መሰንበት ሲችል በአንዲት ከረጢት ደም እጦት ሲሞት ይበልጥ ያማል።

በአዲስ አበባ ካሉ በመደበኛነት ደም ከሚለግሱ ጥቂት ለጋሾች መካከል ኢዜአ ከ65 እስከ 75 ጊዜ ደም በመለገስ ህይወት እያካፈሉ የሚገኙትን አቶ ሐይለአብ አለማየሁን፣ አቶ ደረጀ እንግዳንና አቶ አዲሱ ወልደ ሃዋሪያትን አነጋግሯል።

አቶ ሐይለአብ አለማየሁ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ከ1997 ዓም ጀምሮ ለተከታታይ 18 ዓመታት በፈቃደኝነት ደም ለግሰዋል ።

በአንድ ወቅት ጓደኛቸው ታሞ  በተሰጠው ደም ከህመሙ ሲፈወስ ማየቱ በመደበኛነት ደም ለመለገስ እንዲወስኑ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል ።

ከዛች ዕለት ጀምሮ በየሶስት ወሩ ያለምንም መቆራረጥ ደም ለሚያስፈልጋቸው ደም እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ምንም አይነት የጎንዮሽ የጤና ጉዳት እንደሌለውና ይልቅ በሚለግሱበት ጊዜ የደስታ ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋል ነው ያሉት።

"65 ጊዜ ደም ስለግስ ምንም አይነት የጤና እክል አጋጥሞኝ አያውቅም፤ ይልቅስ የተሻለ ስሜት እንዲሰማኝ ያደርገኛል" ብለዋል።

ሌላኛው በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሽ አቶ ደረጀ እንግዳ በበኩላቸው፣ ከ1989 ጀምሮ 75 ከረጢት ደም ለግሻለሁ ብለዋል። በአንዲት ከረጢት ደም የሰው ህይወት መታደግ በዋጋ የማይታመን  ውስጣዊ የመንፈስ እርካታ እንደሚያስገኝ ገልጸዋል።

"ደም መስጠት ህይወት መስጠት ነው፤  ታዲያ ህይወት ከመስጠት በላይ ምን የሚያስደስት ነገር አለ" ብለዋል።

ሰባ ጊዜ  ደም መለገሳቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ አዲሱ ወልደሃዋሪያት ናቸው።

መቶ ጊዜ ለመለገስ ማቀዳቸውን ገልጸው፣ ሌሎች የሳቸውን ፈለግ ተከትለው ሠዎችን ከህመምና ከሞት የመታደግ ቅዱስ ተግባር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።

ለአብነት እነዚህን ሰዎች እናንሳ እንጂ ከዚህም በላይ ደም የለገሱ ምግባረ ሰናይ ሰዎች መኖራቸው አያጠራጥርም።

ደም መለገስ ሰዎችን ከህመማቸው ከመፈወስና ከሞት ከመመለስ ባሻገር ለጤናማ የደም ዝወውር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ሰዎች ደም ከመለገሳቸው በፊት በሚደረግላቸው ምርመራም ወቅታዊ የጤና ሁኔታቸውን እንዲያውቁ እንደሚያስችላቸውም ይናገራሉ፡፡

ታዲያ በአንድ ድንጋይ ሁለት  ወፍ ማለት ይህም አይደል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም