የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰራተኞች አስተዳደር ደንብን አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰራተኞች አስተዳደር ደንብን አጸደቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2015 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰራተኞች አስተዳደር ደንብን አጽድቋል፡፡
በምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
በዚህም ኢዜአ በሕግ የተሰጠውን ተግባርና እና ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት በዕውቀት፣ክህሎትና ሙያዊ ስነ-ምግባር የተገነባ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ሁኔታዎችን ተገንዝቦ የሚሰራ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እያደገ ከመጣው የሚዲያ ባህሪ ጋር የተናበበ የሰው ኃይል አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቡ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
ረቂቅ ደንቡ ኢዜአ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስከብሩ የይዘት ስራዎችን ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተደራሽ በማድረግ በአፍሪካ ተጠቃሽ የዜና ምንጭ ለመሆን ያስቀመጠው ራዕይ እንዲያሳካ ያግዛል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ግልጽነትና ተጠያቂነት መሰረት ባደረገ መልኩ ብቁ ሰራተኞችን ለመቅጠር፣ለማስተዳደር እና አስፈላጊ ሲሆን ለማሰናበት የሚያስችል አሰራርን ለመዘርጋት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
ሚዲያ ካለው ልዩ ባህሪ አንጻር 24 ሰዓት መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ረቂቅ ደንቡም ይህንን የሚዲያ ልዩ ባህሪ ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
የተቋሙ ሰራተኞች መብትና ግዴታቸውን በውል ለይተው እንዲያውቁና ስራቸውን በኃላፊነት መንፈስ እንዲያከናውኑ እንደሚያደርግም አብራርተዋል፡፡
በረቂቅ ደንቡ ላይ የባለድርሻ አካላት የውይይት እና የአስተያየት መስጫ መድረክ መካሄዱንም አስታውሰዋል፡፡
ምክር ቤቱ ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰራተኞች አስተዳደር ደንብ ቁጥር 2/2015 ሆኖ እንዲጸድቅ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡