የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ አረምን በማስወገድ መሬቱን ለግብርና ልማት ከማዋል ባለፈ ለፋብሪካዎች አማራጭ የኃይል ምንጭ ማድረግ ተችሏል - ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ አረምን በማስወገድ መሬቱን ለግብርና ልማት ከማዋል ባለፈ ለፋብሪካዎች አማራጭ የኃይል ምንጭ ማድረግ ተችሏል - ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ አረምን በማስወገድ መሬቱን ለግብርና ልማት ከማዋል ባለፈ ለፋብሪካዎች አማራጭ የኃይል ምንጭነት ማዋል መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።
የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በበኩሉ ለሲሚንቶ ምርት የሚጠቀመውን የድንጋይ ከሰል ኃይል አስር በመቶ በፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራን መጤ አረም በመተካት የተሳካ የሙከራ ውጤት መገኘቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የበረሃማነትን መስፋፋት ለመከላከል እንደተተከለ የሚነገርለት የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ መጤ አረም አሁን ላይ ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በወረራ ይዟል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋት አርሶ አደሮችን ያለ እርሻ አርብቶ አደሮችን ያለ እንስሳት መኖ አስቀርቷል።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ሴክተር ሪፎርም ፐርፎርማንስ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሳሙኤል ሀላላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፕሮሰሲንግ ጁሊፍሎራ በበቀለባቸው አካባቢዎች ለእንስሳት መኖ የሚሆኑ ሳሮችና ሌሎች ዛፎች እንዳይበቅሉ በማድረግ አርሶና አርብቶ አደሮችን ለችግር ዳርጓቸው ቆይቷል።
በአውሮፓና አሜሪካ አረሙ ለአማራጭ የኃይል ምንጭነት እንደሚውል ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ይህ ጥቅም ላይ ሳይውል መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ መንግስት ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተቋማትና ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መጤ አረሙ ለፋብሪካዎች አማራጭ የሀይል ምንጭነት የሚውልበት የአዋጭነት ጥናት አጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
አረሙን በከፍተኛ የሙቀት ኃይል አማካኝነት የባዮ ማስ አማራጭ ኃይል ሆኖ ለፋብሪካዎች እንደሚያገለግል ነው የተናገሩት፡፡
በመሆኑም ለእርሻ አገልግሎት ምቹ በሆኑ ስፍራዎች የበቀለውን አረም በማስወገድ መሬቱን ለግብርና ልማት ከማዋል ባሻገር ለተለያዩ ፋብሪካዎች ግብዓት ሆኖ እንዲያገለግል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አረሙ ከኃይል አማራጭነት በተጨማሪ ለወረቀት ምርት ግብዓት እንደሚሆንም ነው የተናገሩት፡፡
በአፋር ክልል አሚባራና በሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን 215 ሄክታር መሬት የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ አረም በማስወገድ ለእርሻ ስራ አገልግሎት ማዋል ተጀምሯል ብለዋል።
በተጨማሪም 1ሺህ 600 ቶን መጠን ያለው መጤ አረም በሁለቱ ማሽኖች በመሰብሰብ ለአማራጭ ኃይል ምንጭነት እንዲውል ለፋብሪካዎች ማቅረብ መጀመሩንም ገልጸዋል።
በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ የኢነርጂ ክላስተር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ገዛኸኝ ሃምዛ፤ እስካሁን ባለው የሙከራ ሂደት እስከ አስር በመቶ መጤ አረሙን በሙከራ ደረጃ ለኃይል ግብዓት በመጠቀም ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
መጤ አረሙ ለኢንዱስትሪ ግብዓት መሆን እንደሚችል ማረጋገጣቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ ከድንጋይ ከሰል የሚገኘውን ኃይል እስከ 40 በመቶ በመጤ አረሙ ለመተካት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ አረም አስተማማኝ የኃይል አማራጭ መሆን እንደሚችል የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይ ለሚ ላይ ለሚገነባው የሲሚንቶ ፋብሪካ መጤ አረሙ ለኃይል ግብዓት እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የመጤ አረሙን ለኃይል አማራጭ ለመጠቀም በጀትና የሰው ኃይል መድቦ ለሌሎች ፋብሪካዎች ጭምር ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡
አንድ የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ ዛፍ በቀን ሰባት ሊትር ውሃ እንደሚመጥ የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ እያንዳንዳቸው በቀን ከአራት ሄክታር በላይ አረም ማስወገድ የሚችሉ ሁለት ማሽኖች ያለማቋረጥ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ገዛኸኝ ሃምዛ በበኩላቸው፤ አረሙ ካለው መጠነ ሰፊ ስርጭት አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለቀጣይ 50 ዓመታት እስከ 60 በመቶ የሚሆናቸውን አማራጭ ሃይል ከዚሁ አረም ማግኘት እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡