ቀጥታ፡

የአፍሪካ የስራ ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2015(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ የስራ ፈጠራ ፎረም በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።

ፎረሙ እየተከናወነ የሚገኘው "በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ገበያ የስራ ፈጠራ፣ የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን ማፋጠን" በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

በፎረሙ ላይ የኢፌዴሪ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የአፍሪካ ሕብረት የንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ሞኒክ ንሳንዛባንጋዋ እና የአፍሪካ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የአፍሪካ የስራ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች እንግዶች ታድመዋል።

በፎረሙ በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን ትግበራ፣ ለአፍሪካ ወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ እና የአፍሪካ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት ጥምረት ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት ይደረጋል።

ፎረሙ ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የስራ እድል ፈጠራ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ እና ሌሎች ተያያዥ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የጎንዮሽ እና የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ።

የአፍሪካ የስራ እድል ፈጠራ ፎረም አካል የሆነው የአፍሪካ ትስስር ቀንም በመከበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም