ቀጥታ፡

የእጅ ስልክን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል መሙላት የሚያስችል የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ሲስተም ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2015(ኢዜአ)፦ የእጅ ስልክን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል መሙላት የሚያስችል የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ሲስተም ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ተፈርሟል።

የፕሮጀክት ግንባታ ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ኢንህሜትር ካምፓኒ ናቸው።

ስምምነቱ ባለፉት 15 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ቴክኖሎጂ በስማርትና ኤስ.ቲ.ኤስ ቶክን ቴክኖሎጂ ለመተካት የሚስችል የፕሮጀክት ትግበራ መሆኑም ታውቋል፡፡


 

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ እንደተናገሩት በስራ ላይ ያለው የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ አገልግሎት ለደንበኞች አመቺ ስላልሆነ ካምፓኒው በገባው ውል መሰረት የዘመናዊ ፕሮጀክት ትግበራውን በጥራት አጠናቆ እንዲያስረክብ አሳስበዋል፡፡

የቻይናው ኢንህሜትር ካምፓኒ ሊሚትድ ቴክኒካል ዳሬክተር ሚር ዲንግ ፉሚን በበኩላቸው የፕሮጀከት ስራውን በጥራትና በወቅቱ አጠናቀው እንደሚያስረክቡ ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክት ትግበራው 5 ሚሊዮን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል የስማርት ቅድመ ክፍያ የአይ ሲቲ ሶፍትዌርና መሰረተ-ልማት እቃዎች አቅርቦት ትግበራ መሆኑም ተገልጿል

በተጨማሪም የ5 መቶ ሺህ ነጠላና ሶስት ፌዝ የስማርት የኤስ.ቲ.ኤስ ቆጣሪና ተያያዥ እቃዎች አቅርቦት እንዲሁም የቴክኒክና የሲስተም አጠቃቀም ስልጠና እና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን የሚያካትት ነው፡፡


 

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ደንበኞች በእጅ ስልካቸው፣ በዲጂታል ክፍያ አማራጮች፣ በባንክ ኤ ቲ ኤም ማሽኖች፣ ከተቋሙ ጋር በሚሰሩ ወኪል ሱቆች፣ በተቋሙ የጥሪ ማዕከሎች አማካኝነት የኤሌክትሪክ ኃይል በቀላሉ መሙላት ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ ከቆጣሪ ጋር ተያይዞ የሚከሰትን የኃይል ብክነት ለመቀነስ፣ የንባብ፣ የቢልና የገንዘብ አሰባሰብን ለማዘመን እና ገቢን ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

የፕሮጀክቱ ትግበራ አጠቃላይ ወጪ 48 ሚሊዮን 875 ሺህ 545 የአሜሪካን ዶላር መሆኑም ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የፕሮጀክቱ የሶፍትዌር ትግበራ በስድስት ወራት የሚጠናቀቅ ሲሆን የ500 ሺህ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች አቅርቦት እና ትግበራ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም