ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2015(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሶስተኛ ቀን ውሎ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በመርሐ-ግብሩ መሰረት ወላይታ ድቻ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ወላይታ ድቻ በ37 ነጥብ 12ኛ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ በ57 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ወላይታ ድቻ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ በሁለቱ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ባህር ዳር ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል፤ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።


 

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ሌላኛው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን እና ሀዲያ ሆሳዕናን ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ያገናኛል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ መድን በ49 ነጥብ ሶስተኛ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና በ40 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ባደረጋቸው ያለፋት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንዱን አሸንፎ በሁለቱ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ሀዲያ ሆሳዕና ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ በሁለቱ ተሸንፏል፤አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም