ቀጥታ፡

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ መሬትን 20 ሚሊየን ሄክታር ለማድረስ እየተሰራ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ መሬትን በቀጣይ አመት 20 ሚሊየን ሄክታር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ እድገት ውስጥ 6 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ሊያመጣ እንደሚችል ጠቁመው፤ በዚህም በሄክታር ከ40 ኩንታል የማይበልጠውን ምርታማነት ወደ 70 እና 80 ኩንታል ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግም ለዘንድሮው የመኸር የግብርና ልማት 15 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈፀሙንም አስረድተዋል።

ከዚህም ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ ሲሆን ቀሪውም በመጓጓዝ ላይ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም 178 ሚሊዮን ሜትር ኩዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን እና በአሲድ የተጠቃን 7 ሚሊዮን ሔከታር መሬት በኖራ ለማከም አምስት ዝቅተኛ አቅም የኖራ ማምረቻ ፋብሪካዎች መቋቋማቸውን ገልጸዋል።

ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረትም ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ብቻ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ከመደረጉ ባሻገር 180 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።

በግብርናው ዘርፍ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ ከዚህ ቀደም ያልታረሰ መሬትን በማረስ፣ በአሲድ የተጠቃ መሬትን በኖራ ማከም እየታረሰ የሚገኘውን 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የማስፋት እቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።

በዚህም የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ የእርሻ መሬትን በቀጣይ ዓመት 20 ሚሊየን ሄክታር ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከስራ እድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ መንግስት በ2015 በጀት ዓመት በ11 ወራት ለ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አንስተዋል።

ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮኑ በግብርና 600 ሺህ ገደማ ደግሞ በኢንዱስትሪዎች የስራ እድል ያገኙ ናቸው ብለዋል።

በሌሎች ዘርፎችም በርካታ ዜጎች የስራ እድል ማግኘታቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ 100 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ ህጋዊ በሆነ መንገድ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አድርገዋል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ እድገት 7 ነጥብ 5 በመቶ የሚመዘገብበት ይሆናልም ብለዋል።

ለዚህም ከጥቅል ምርት 33 በመቶ ድርሻ የሚይዘው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ 6 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብና ለዚህም የሰብል ምርቶች ሚና የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ 28 በመቶ መሆኑን በማንሳት በዚህ በጀት ዓመት 8 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት እንደሚያመጣ ይጠበቃል ብለዋል።

በኢንዱስትሪው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስራ አቁመው የነበሩ 160 ፋብሪካዎችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።

ከጥቅል ሀገራዊ ምርት 39 በመቶ ድርሻ ያለው የአገልግሎት ዘርፉ ከቱሪዝም፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎች ንዑስ ዘርፎች በሚገኘው ውጤት 7 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ መተንበዩን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የምክር ቤቱ አባላት በግብርና ልማት፣ በሰላምና ጸጥታ፣ የኑሮ ውድነት፣ የስራ እድል ፈጠራ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም