ቀጥታ፡

በተለያዩ ኬላዎች ላይ የሚሰሩ 15 የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ሰራተኞች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ 

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015(ኢዜአ)፦በተለያዩ ኬላዎች ላይ የሚሠሩ 15 የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ሠራተኞች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ። 

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት ከሕብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በጋራ በመተባበር በጅማ በር፣ በወለጋ በር፣ በደሴ በር፣ በቱሉ ዲምቱ በር፣ በጎጃም በር፣ በአቃቂ በር እና በቢሾፍቱ በር፣ በቡሌ ሆራ በር ፣ በአገረማርያም በር እና በሌሎች ኬላዎች ባደረጉት ኦፕሬሽን መሆኑን ገልጿል።

በኦፕሬሽኑም የተለያዩ አገራት ገንዘብ እና ብር እንዲሁም ሕገ-ወጥ ሽጉጦችና ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከመሰል ጥይቶች ጋር መያዛቸውን አመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ኬላዎች ላይ ተመድበው በሚሰሩበት ወቅት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ወደ ውጭ የሚላከውን ቡና ከመነሻው እስከ መድረሻ መዝግበው እንዲያስተላልፉ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከአንዳንድ ላኪ ነጋዴዎች ጋር ትስስር ፈጥረው ገንዘብ በመቀበል ቡናውን ሳይመዘግቡ ከአሰራር ስርዓት ውጪ በማድረግ ሲያስተላልፋ እንደነበር ነው የምርመራ ቡድኑ የገለጸው። 

ግለሰቦቹ ወደ ውጭ አገር መላክ ያለበትን ቡና በሕገ-ወጥ መንገድ በአገር ውስጥ እንዲሸጥ በማድረግ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ በማሳጣት ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ሕብረተሰቡ ለፀጥታ አካላቱ ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን የተለመደ ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም