ቀጥታ፡

መራመድን በመናፈቅ ለተሻለ ሕይወት ተስፋን የሰነቁ እግሮች

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015(ኢዜአ)፦ ወይዘሮ ምሳዬ እሸቱ ኑሮን ለማሸነፍና ሕይወታቸውን በተሻለ የገቢ አቅም ለመምራት ሕልም ሰንቀው ለ10 ዓመታት ያህል በሳዑዲ አረቢያ በስደት ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ ማን እንደ አገር ... እንዲሉ የስደት ሕይወታቸው እንዳሰቡት ምቹ መሆኑ ቀርቶ ለድካምና ለጤና እክል መዳረግ የሕይወት ዕጣ ፈንታ እንደሆነባቸው ያስታውሳሉ።

በስደት የተባባሰ ህመም ይዘውት የመጡት የእግር ሕመም እየተባበሰ መጥቶ ሥራቸውን በቀላሉ እንዳያከናውኑ ከፍተኛ እንቅፋትና ፈተና እንደሆነባቸው ይገልጻሉ።

በነበረባቸው የስራ ጫናም ''እግሬን በወቅቱ ባለመታከሜ የደም መርጋት ሕመም አጋጥሞኛል፤ ችግሩም እየተባባሰ መጥቶ ወደ አገር ቤት እንድመለስ አስገድዶኛል'' ሲሉ የሕይወት ውጣ ውረድ ገጠመኛቸውን ይናገራሉ።

ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋም ለእግራቸው ሕክምና በተለያየ ጊዜ ገንዘብ ወጪ አድርገው ለመታከም ጥረት ቢያደርጉም ተስፋ በመቁረጥ መፍትሔ ሳያገኙ መቅረታቸውን ያነሳሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተደረገላቸው ሕክምና አንድ እግራቸው መቆረጥ ስላለበት በመታመኑ ተቆረጠ ይላሉ።

በሆስፒታሉ የአካል ተሐድሶ ማዕከል የእግር ድጋፍ ሕክምና ተሰርቶላቸው በልምምድ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የተደረገላቸው ድጋፍ ''የከሰመው ተስፋዬ እንደገና እየለመለመልኝ ነው'' ብለዋል ወይዘሮ ምሳዬ ።

በስደት አገር ባጋጠማቸው የስራ ጫና ጉዳት ያጋጠመው እግራቸውን ቢያጡም ምትክ የእግር ድጋፍ ማግኘታቸው ሕይወትን በተሻለ መንገድ ለመምራት የሚያስችል አስደሳች ክስተት መሆኑን ገልጸዋል።

በስኳር ሕመም ምክንያት አንድ እግራቸውን እንዳጡ የሚያስታውሱት ደግሞ አቶ ደጉ አንድሰው ናቸው።

በሕይወት ለመቆየት እግራቸው መቆረጥ የግድ ያለበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ።

በስተርጅና አካል ጉዳተኛ መሆንን አምኖ መቀበል ከባዱ የሕይወት አጋጣሚ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአካል ተሐድሶ ማዕከል ምትክ የአካል ድጋፍ ማግኘታቸው ''የቀደመ ሕይወቴን እንድናፍቅና ያጋጠመኝን ችግር እንድረሳ አድርጎኛል'' ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአካል ተሐድሶ ማዕከል ለዓመታት ያቋረጠውን የሕክምና አገልግሎት እንደገና ዛሬ ጀምሯል።

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዷለም ደነቀ እንዳሉት፤ ማዕከሉ ዳግም የተመለሰው ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እና ጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተደረገው ጥረት መሆኑን ገልጿል።


 

ማዕከሉም ለአካል ድጋፍ የሚውሉ ግብዓቶችን ማምረት ጨምሮ በዘርፉ የሚሰሩ የሕክምና ባለሙያዎችን ማሰልጠን እንዲያስችል ተደርጎ በአዲስ መልክ መደራጀቱን ተናግረዋል።

በአካል ድጋፍ መንቀሳቀስ እየቻሉ ዕድሉን ላላገኙ አካል ጉዳተኛ ዜጎችም እፎይታን የሚቸር ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አገልግሎቱም በነጻ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።


 

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ፤ "በኢትዮጵያ አብዛኛው አካል ጉዳተኛ ለኑሮ ምቹ ያልሆነ ሕይወት እየመራ ይገኛል" ብለዋል።


 

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተሐድሶ ማዕከል በድጋሚ መቋቋሙ ፌዴሬሽኑ ለዘመናት ሲያቀርብ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎቱም አካል ጉዳተኞች በሚደረግላቸው እገዛ እንዲንቀሳቀሱ እና አምራችነታቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችልና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ቀና ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም