ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጅግጅጋ ከተማ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጅግጅጋ ከተማ ተጀመረ
ጅግጅጋ ሰኔ 29 /2015(ኢዜአ) ፡- ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መረሃ ግብር ዛሬ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተጀመረ።
ከሐረር የተነሱት ወጣቶቹ መረሃ ግብሩን የጀመሩት "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ !" በሚል መሪ ሀሳብ በጅግጅጋ ከተማ የወጣቶች ማዕከል እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ነው።
የብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌ በወቅቱ ፤ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች ተወልደው ካደጉበት ማኅበረሰብ ወጥተው ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ የሌላኛውን ማኅበረሰብ ባህልና ወግ እንዲያውቁ ያስችላል ብለዋል ።
ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ያካሄዱት የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከተሞችን በጋራ አረንጓዴ የማድረጉ ጥረት አካል እንደሆነ ተናግረዋል።
በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች ያከናውኗቸው ስራዎች የህዝቡን አንድነትንና ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክር በመሆኑ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ዩሱፍ መሀመድ በበኩሉ፤ ዛሬ በክልሉ የተጀመረው የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የህዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሻሻል እንደሚያግዝ ገልጿል።
በመረሃ ግብሩ መሰረት በወጣቶቹ ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል ችግኝ ተከላ፣ ደም ልገሳ፣ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠትና የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት ይገኝበታል ብሏል።
ወጣት ሱሌኻ አብዲ አህመድ የመረሃ ግብሩ ተሳታፊ ሲሆን፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራው ላይ የተሳተፈው የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈታ በማገዝ የድርሻውን ለመወጣት መሆኑን በሰጠው አስተያየት ገልጿል።
በማስጀመሪያው ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ማህዲ አዳን፣የብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ፋይሰል ረሺድ፣የጅግጅጋ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ ኢንጂነር ሲያድ አብዲን ተገኝተዋል።