የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት እና የኢዜአ አመራርና ሰራተኞች በሞጆ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት እና የኢዜአ አመራርና ሰራተኞች በሞጆ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015(ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አመራርና ሰራተኞች በጋራ በሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የችግኝ ተከላ አካሄዱ።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፤ ድርጅቱ የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ምርቶች ከማሳለጥ በተጨማሪ የአረንጓዴ አሻራና እና የአካባቢ ጥበቃ ላይ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ዓመት 12 ሺህ ችግኞችን የመትከል እቅድ መያዙን ገልጸው በሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ዛሬ ጀምረናል ብለዋል።
ድርጅቱ የወጪና ገቢ ምርቶችን ከማሳለጥ ባለፈ በደረቅ ወደቦችና ተርሚናሎች የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከልማት ስራዎቹ አንዱ የአረንጓዴ አሻራ ልማት መሆኑን ጠቅሰው የተራቆቱ አካባቢዎችን በመረከብ እያለማ መሆኑን ገልጸዋል።
የድርጅቱ ምክትል ስራ አስፈጻሚ ወንድሙ ደምቦ፤ ድርጅቱ የአረንጓዴ አሻራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ80 ሺህ በላይ ችግኞች መትከሉን ገልጸዋል።
የችግኞች እንክብካቤና አረንጓዴ የማድረግ ስራም እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢዜአ የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ዳይሬክተር ዮሐንስ ወንዲራድ፤ ኢዜአ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ተግባሩ በተጨማሪ የአረንጓዴ አሻራ በማኖር የበኩሉን እየተወጣ ይገኛልም ነው ያሉት።
የሞጆ ከተማ ምክትል ከንቲባ እሸቱ ተሾመ፤ በከተማ አስተዳደሩ በዚህ ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በከተማዋ ከሚገኙ የድርጅቶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ችግኞችን የመትከል ንቅናቄ ተጀምሯል ብለዋል።