በኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ገበያ ሲጀመር ለፋይናንስ ሴክተሩ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው- የኢሲኤ ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ገበያ ሲጀመር ለፋይናንስ ሴክተሩ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው- የኢሲኤ ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015(ኢዜአ) ፡ በኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ገበያ ሲጀመር ለፋይናንስ ሴክተሩ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን/ኢሲኤ/ ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ)፣ ዓለም አቀፍ የባንኮች ሴክተርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ፤ በቀጣዩ ዓመት የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ግብይትን እውን ለማድረግ ሰፊ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን መቋቋም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ውስጥ የመንግሥት ቁልፍ አቅጣጫ መሆኑን በማንሳት የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ገበያም በዚሁ ውስጥ የተካተተ ነው ብለዋል።
የካፒታል ገበያ የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ በመደገፍ በዘላቂ የልማት ግብ ትልቅ ሚና የሚኖረው መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰነደ መዋዕለ-ንዋይም ከዚሁ ጎን ለጎን የሚተገበር ይሆናል ብለዋል።
በዋናነትም ግብይቱ በተቋማት የኢኮ ሲስተም መስክ፣ በካፒታል ገበያ ተግባራዊነትና መሰል ተግባራት ሁለቱም ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ይሆናሉ ብለዋል።
በዚህም የገበያውን ግንዛቤ በማሳደግ፣ የኢንቨስተሩን ፍላጎት በመጨመር፣ የገበያ ሳቢነት በመፍጠርና የካፒታል ገበያውን ግንዛቤ በማሳደግ በኢኮኖሚው ውስጥ የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ፤ መድረኩ ለኢትዮጵያ የሰነደ መዋለ ነዋይ ምስረታ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በአፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላትና የአህጉሪቷ የፖለቲካ ማዕከል በሆነችው ኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ- ንዋይ ገበያ መጀመር ትልቅ ትርጉም ያለውና ለፋይናንስ ሴክተሩም አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም የመንግሥታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት የሪፎርም አጀንዳ እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ለተግባራዊነቱ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
''በኢትዮጵያ የመዋዕለ-ንዋይ ግብይት ፕሮጀክት ማናጀር ሚካኤል ሐብቴ፣ ከወራት በፊት የግብይቱን መቋቋም እውን ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማድረግና ለሕዝቡም ግንዛቤ የመስጠት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአፍሪካ የፋይናንስ ሴክተር የካፒታል ገበያ ስፔሻሊስት ቪክቶር ኒኪሪ፤ በአፍሪካ ከ30 በላይ ሀገራት ላይ ትኩረት ያደረገ የዘርፉ የፕሮጀክት ቀረፃ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን አንዷ ቁልፍ የዘርፉ አካል በማድረግ ለግብይቱ ተግባራዊነት እገዛ እያደረግን እንገኛለንም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2024 ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ባለው የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ግብይት ''ለኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ግብይት ለካፒታል ገበያ የኢኮ-ሲስተም የአቅም ግንባታ'' በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው እለት የውይይት መድረክ ተደርጓል።