ቀጥታ፡

የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና የተሻለ የፈተና ዝግጅት እንድናደርግ አነሳስቶናል----የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተፈታኝ ተማሪዎች

ደሴ ሰኔ 29/2015 (ኢዜአ)፡-የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ባለፉት ዓመታት የተማሩትን ጭምር በመከለስ ለፈተናው በተሻለ እንዲዘጋጁ ያነሳሳቸው መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተፈታኝ ተማሪዎች ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ ተማሪዎች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ አስፈላጊውን የቅደመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን አስታውቋል።

በዩኒቨርሲቲው የህግ ተማሪ ኡቻን ሮድዶ ለኢዜአ እንደገለጸው የመውጫ ፈተናውን በላቀ ውጤት ለማለፍ ዓመቱን ሙሉ ዝግጅት አድርጓል።

በእዚህም ባለፉት ዓመታት የተማራቸውን ኮርሶች ጭምር በማጥናትና በመከለስ መዘጋጀቱን የጠቀሰው ተማሪው፣ መምህራንም በማካካሻ ትምህርት ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ተናግሯል።

የመውጫ ፈተናው በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ምን ያህል እውቀት እንዳገኙ ራሳቸውን የሚፈትሹበት መሆኑን ጠቁሞ፣ "እንደሀገር ብቁ የሰው ሀይል ለማፍራትም ፋይዳው የጎላ ነው" ብሏል።

"መውጫ ፈተናው ጥራት ያለው፣ በአግባቡ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እንደሀገር የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ ደስ ብሎናል፣ እኛም ለፈተናው በተሻለ እንድንዘጋጅም አድርጎናል" ብሏል።

እርሱም በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ያገኘውን እውቀት ተጠቅሞ ፈተናውን ለማለፍ ዝግጅት ማደረጉንና ይህም ቀጣይ በሥራ ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዘው አመልክቷል።


 

የመውጫ ፈተናው ጠንከረው እንዲማሩና እንዲያጠኑ ማድረጉን የተናገረው ደግሞ የዩኒቨርሲቲ የትምህርት እቅድና ሥራ አመራር ትምህርት ክፍል ተማሪ ፉዓድ ሱነሞ ነው።

"በተለይ ባለፉት ዓመታት ጭምር የተማርናቸውን ከልሰን ማንበባችን እውቀትና ክህሎታችንን ለማስፋት ረድቶናል" ብሏል።

"የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና መጀመሩ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ያግዛል፤ ጥሩ ጅምር ነው" ያለው ተማሪው፤ በፈተናው የላቀ ውጤት ለማምጣት ለወራት መዘጋጀቱን ገልጿል። 

ዩኒቨርሲቲው በኦን ላይን ፈተና በቂ ልምድና ዝግጅት እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጾ፣ በተሰጣቸው የማካካሻ ትምህርትና በግሉ ለፈተናው በቂ ዝግጅት ማድረጉን ጠቁሟል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አወል ሰይድ በበኩላቸው እንዳሉት በመውጫ ፈተናው ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመጡትን ጨምሮ ከ7 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ለማስፈተን ዝግጅት ተደርጓል።


 

ዶክተር አወል እንዳሉት፣ ከእነዚህ ተፈታኞች መካከል ከ2 ሺህ 500 የሚበልጡት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው።

ተማሪዎች በመውጫ ፈተናው ውጤታማ ሆነው ተወዳዳሪና ብቁ መሆን እንዲችሉ የማካካሻ ትምህርት በመስጠት እና ስነ ልቦናቸውን በመገንባት ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል።

ለፈተና የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ማዘጋጀትን ጨምሮ ተማሪዎች በኦን ላይን የመለማመጃ ፈተና ወስደው በቂ ዝግጅት እንዲደርጉ መሰራቱንም ጠቁመዋል።   

ፈተናው ተማሪዎች የተማሩትን መለስ ብለው እንዲያስታውሱ ከማድረግ ባለፈ እንደ ሀገር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑንም ዶክተር አወል አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከመጪው ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ይሰጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም