ቀጥታ፡

አርባ ምንጭ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ወረደ 


አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015(ኢዜአ)፦ አርባ ምንጭ ከተማ በ2015 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የወረደ ሶስተኛው ክለብ ሆኗል።

በፕሪሚየር ሊጉ የ30ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ወሳኝ የሆኑ ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት በአዳማ ከተማ ተካሄደዋል።


 

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ እና አዳማ ከተማ አንድ አቻ ወጥተዋል።


 

አቤል ነጋሽ ለወልቂጤ ከተማ እንዲሁም አድናን ረሻድ ለአዳማ ከተማ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ እና አርባ ምንጭ ከተማ አንድ እኩል ወጥተዋል።

እዮብ ዓለማየሁ ለሃዋሳ ከተማ ሲያስቆጥር አህመድ ሁሴን ለአርባ ምንጭ ከተማ ግቡን ያስቆጠረ ተጫዋች ናቸው። 

ውጤቶቹን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ በ35 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ በፕሪሚየር ሊጉ መቆየቱን ሲያረጋግጥ በአንጻሩ አርባ ምንጭ ከተማ በ34 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ከፕሪሚየር ሊጉ ወርዷል።

አርባ ምንጭ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ለገጣፎ ለገዳዲ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የወረደ ሶስተኛ ክለብ ሆኗል።

ሻሸመኔ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማደጋቸው ይታወቃል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር መቻል ከለገጣፎ ለገዳዲ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም