በየዓመቱ ለሳተላይት መረጃ ይወጣ የነበረውን 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ማስቀረት ተችሏል- የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በየዓመቱ ለሳተላይት መረጃ ይወጣ የነበረውን 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ማስቀረት ተችሏል- የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015(ኢዜአ) ፡ የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት አገልግሎት ላይ በመዋሉ በየዓመቱ ለሳተላይት መረጃ ይወጣ የነበረውን 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ማስቀረቱን የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት የምህንድስና ዲዛይን የሚሰራበትን ሂደት የሚያሳይ መጽሐፍና የሳተላይት መተግበሪያ ይፋ አድርጓል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ፤ የኢትዮጵያን የቆዳ ስፋት የሚሸፍን 2 ሜትር የሳተላይት ጥራት (ሪዞሉሽን) ያለው መረጃ እንደ አገር እየተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በዓመት ለሳተላይት መረጃ የምታወጣውን 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር አስቀርቷል ብለዋል።
የሳተላይት መረጃ ለተፈጥሮ ኃብት አስተዳደር፣ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማትና ለተረጋገጡ መረጃዎች የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም አስረድተዋል።
የሳተላይት መረጃዎች የተፈጥሮ አደጋን ቀድሞ ለመከላከልና ወቅታዊ መረጃዎችን በማግኘት ለአገር ልማትና እድገት ያለውን አስተዋጽዖም ጠቅሰዋል።
በታኅሳስ 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን "ኢቲ አር ኤስ ኤስ-01" የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ሕዋ መላኳ ይታወሳል።
በታኅሳስ 2013 ዓ.ም ደግሞ "ኢቲ-ስማርት-አር ኤስ ኤስ" የተሰኘችውን ሁለተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በተመሳሳይ አምጥቃለች።
ሁለቱም ሳተላይቶች ግብርና፣ የመሬት አስተዳደር፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የተፈጥሯዊ አደጋዎችና ሌሎች ተጓዳኝ መረጃዎችን ተደራሽ የሚያደርጉ መሆኑ ይታወቃል።
የምህንድስና ዲዛይን የሚሰራበትን ሂደት ለማሳየት ይጠቅማል በሚል የተዘጋጀው መጽሐፉም ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
የተዘጋጀው መጽሐፍ የምህንድስና ዲዛይንን ይዘትና ውጤቱን የሚያስረዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሲስተም ኢንጂነሪንግ ትግበራን እውን ለማድረግና ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።