የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአርባምንጭ ከተማ ከ1 መቶ 80 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን የደቡብ ሬጅመንት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ካምፕ አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአርባምንጭ ከተማ ከ1 መቶ 80 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን የደቡብ ሬጅመንት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ካምፕ አስመረቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አርባምንጭ ከተማ ከ1መቶ 80 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን የደቡብ ሬጅመንት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ካምፕ አስመረቀ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከጀመረው የሪፎርም ሥራዎች አንዱ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በከፍተኛ ደረጃ በማደራጀትና ለግዳጅ ማብቃት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በሀገሪቱ አራቱም ማዕዘናት እና በተመረጡ የወታደራዊ ፖሊስ ስትራቴጂክ ቦታዎች ላይ ሰፋፊ የግንባታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ለግንባታው መጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ ለክልሉ ህዝብና መንግስት እንዲሁም ለድርጅቶች ምስጋና አቅርበው ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት እየጠበቁ ላሉ የደቡብ ሬጅመንት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባላት ስጦታ አበርክተዋል።
የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳደር አቶ ትቆ ትላንቴ በበኩላቸው በአርባምንጭ ከተማ የተገነባው የደቡብ ሬጅመንት ፈጥኖ ደራሽ ካምፕ የአከባቢውን ሰላም ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የጋሞ ህዝብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥነ-ሥርዓት ለሀገር ሰላምና አንድነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተው ግንባታው ዞኑ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት በመሆኑ ወደ አካባቢው ለሚመጡ ቱሪስቶች ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል።