ቀጥታ፡

በመንግስት ጥረት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015(ኢዜአ)፦  በመንግስት ጥረት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በነበሩ ችግሮች 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አስታውሰዋል።

መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በሰራው ስራ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ጠቅሰው አሁንም ከ1 ሚሊዮን የሚበልጡ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአንዳንዶች ዘንድ የጠባቂነትና የተረጂነት ስነልቦና የማዳበር አዝማሚያ መኖሩን አንስተው ለኢትዮጵያውያን የሚጠቅመው ለሚያጋጥሙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት መሆኑን ነው የገለጹት።

ለአብነትም በቦረና አጋጥሞ የነበረውን ድርቅ በመደጋገፍ በማለፍ ዛሬ በቦረና በተሰራ የግብርና ስራ በተለይ በስንዴ ምርት ውጤት እየተገኘ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ከሚያጋጥሙን ችግሮች ፈጥኖ መውጣትን የሁል ጊዜ ልምምድ ማድረግ አለብን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያንን መሸከም የማይችል የኢትዮጵያ አካባቢ መኖር የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ወደ ቀያቸው ያልተመለሱ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም መረባረብ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም