ቀጥታ፡

የራሱን ገቢ የሚያስገባ እና በራሱ ገቢ ወጪውን የሚያስተዳድር ሃገር ነው ነፃ ሀገር የሚባለው--ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015(ኢዜአ)፦ የራሱን ገቢ የሚያስገባ እና በራሱ ገቢ ወጪውን የሚያስተዳድር ሃገር ነው ነፃ ሀገር የሚባለው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 28ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከገቢና ወጪ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተው ምላሽና ማብራሪያቸው ባላፉት 11 ወራት 365 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ገልጸው ይህም ካለፈው በጀት ዓመት 26 ነጥብ 1 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ብለዋል።

በተጨማሪም ባላፉት 11 ወራት 574 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ መውጣቱንና ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ወጪ አንጻር ሲታይ የ13 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የገቢና ወጪ ክፍተቱን ለማጥበብም በታክስ አስተዳደር ላይ ሰፊ ስራዎች መሰራት እንደሚገባ በማከል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የኢትዮጵያ የኢ-መደበኛ ኢኮኖሚ ሰፊ ስለሆነ፣ ገቢ ላይ ሰፊ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም ገልጸዋል።

የሀገራችን የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ከ10 በመቶ በታች መሆኑን ገልጸው የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት 16 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የራሱን ገቢ የሚያስገባ እና በራሱ ገቢ ወጪውን የሚያስተዳድር ሃገር ነው ነፃ ሀገር የሚባለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየለመኑ ነፃነትን ማስቀጠል አይቻልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም