ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን እድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ የተረጋገጠ እውነታ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እሕመድ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን እድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ የተረጋገጠ እውነታ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ባለበት ወቅት ስለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ እድገት 7 ነጥብ 5 በመቶ የሚመዘገብበት ይሆናልም ብለዋል።

ለዚህም ከጥቅል ምርት 33 በመቶ ድርሻ የሚይዘው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ 6 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብና ለዚህም የሰብል ምርቶች ሚና የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

በስንዴ ምርት ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሚሆን ምርታማነት መመዝገቡን ጠቅሰው ዘንድሮ በሩዝ ምርት ይደገማል ብለዋል።

የሌማት ትሩፋትን መርሃ-ግብርን ለማስፋፋትም አምና 26 ሚሊዮን ጫጩት ተሰራጭቶ እንደነበር በማንሳት ዘንድሮ ከ40 ሚሊዮን በላይ ጫጩት ተሰራጭቷል ነው ያሉት።

በፍራፍሬ ልማትም እመርታ እየተመዘገበ ሲሆን በተለይ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ውጭ እስከመላክ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ 28 በመቶ መሆኑን በማንሳት፤ በዚህ በጀት ዓመት 8 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት እንደሚያመጣ ይጠበቃል ብለዋል።

የዘርፉ እድገት ዋነኛ ምንጭ የሆነው ኢንዱስትሪው ለአንድ ዓመት ያህል በተተገበረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስራ አቁመው የነበሩ 160 ፋብሪካዎችን ወደ ስራ ማስግባት መቻሉን ተናግረዋል።

ከጥቅል ሀገራዊ ምርት 39 በመቶ ድርሻ ያለው የአገልግሎት ዘርፉ ከቱሪዝም፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎች ንዑስ ዘርፎች በሚገኘው ከፍተኛ ውጤት 7 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ መተንበዩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተፅዕኖ ውስጥ እንደሚጓዝ መገንዘብ እንደሚገባም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዘንድሮ 6 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ መተንበዩን ጠቅሰው ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ከፍተኛው ዕድገት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም