ቀጥታ፡

በ2016 ዓ.ም 7 ነጥብ 5 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ይጠበቃል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/ 2015 (ኢዜአ)፦ በ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 7 ነጥብ 5 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 28ኛ መደበኛ ስብስባውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመንግስት የ2015 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ቀላል የማይባል እድገት መመዝገቡን ገልጸው የወረስናቸውን እዳዎች እና የፖለቲካ ስብራት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) በኢትዮጵያ እድገት ባለፈው ዓመት 6 ነጥብ 4 ዘንድሮው 6 ነጥብ 1 በመቶ እና የሚቀጥለው ዓመት ደግሞ 6 ነጥብ 4 በመቶ ይሆናል ብሎ መተንበዩን አመልክተዋል።

እኛ በ2016 የምንጠብቀው እድገት 7 ነጥብ 5 በመቶ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዋጋ ንረት ዋና ፈተናችን ነው ብለዋል።

በ2015 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ6 ነጥብ 1 በመቶ መመዝገቡን አስታውሰዋል።

እንደ አገር ያጋጠመውን የኑሮ ውድነት ለመግታት ወደ ገበያ የተረጨውን ገንዘብ ለመቆጣጠር መንግስት በትኩረት እንደሚሰራም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም