ቀጥታ፡

የፋይናንስ  አቅራቢ ድርጅቶች ቀልጣፋ አሰራር አለመሆን የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንቅፋት ሆኗል--ቢሮው

ባህር ዳር  ሰኔ 29/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል አንዳንድ አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማትና አቅራቢ ድርጅቶች ቀልጣፋ አገልግሎት አለመስጠት ለአርሶ አደሩ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ እንቅፋት መፍጠሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የእርሻ ሜካናይዜሽን ስርጭት ግምገማ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው እንደገለጹት፣ በክልሉ የአርሶ አደሩን ድካም የሚቀንሱ የእርሻ ሜካናይዜሽኖችን ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

የግብርና አሰራርን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ልፋት ለማቃለል የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም አሁንም በርካታ መሰራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፉን ለማዘመን በተሰራው ሥራ 1 ሺህ 500 ትራክተሮች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንም ጠቁመዋል

ይህንን ጅምር ሥራ ዘንድሮ አጠናክሮ ለማስቀጠል በክልሉ መንግስት 30 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ አቅራቢ ድርጅቶች ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች እንዲያቀርቡ እየተደረገ ይገኛል።

በተያዘው ዓመት 412 ትራክተሮችን ለመግዛት ታቅዶ ወደሥራ መገባቱን ያስታወሱት አቶ አጀበ፣ እስካሁንም 327ቱ መገዛታቸውንና 175ቱ ደግሞ ለአርሶ አደሮች መተላለፋቸውን ገልጸዋል።

ግዥ የተፈጸመባቸው ቀሪዎቹ ትራክተሮች ለአርሶ አደሩ ለማስተላለፍ በሂደት ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

አንዳንድ የፋይናንስ ተቋማትና አቅራቢ ድርጅቶች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት አለመቻል የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ፈጥኖ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት መሆኑንም አቶ አጀበ አስታውቀዋል።

የግምገማ መድረኩ የገጠሙ ችግሮች ላይ በጋራ መክሮ ለቀጣይ ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በጋራ የማስቀመጥ ዓላማ እንዳለውም አስረድተዋል።

እንደ አቶ አጀበ ገለጻ በክልሉ ለትራክተር እርሻ ምቹ ከሆነው 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ በትራክተር እየታረሰ ያለው ከ20 በመቶ የማይበልጥ መሬት ብቻ ነው።

"በአብዛኛው የግዥ ጥያቄ የሚቀርበው ከግማሽ ዓመት በኋላ በመሆኑ የትራክተሮች ግዥ እንዲዘገይ አድርጓል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባህር ዳር ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አንማው ገዳሙ ናቸው።

እንዲሁም በየጊዜው የማሽነሪዎች ዋጋ መለዋወጥና ደንበኞች መቆጠብ የሚጠበቅባቸውን የገንዘብ መጠን በወቅቱ አለመቆጠባቸው ሌላው ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን ፈጥኖ ገዝቶ በማቅረብ ለታለመላቸው ዓላማ ለማዋል ሁሉም አካል ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም አመልክተዋል።

የአማራ ባንክ ሰሜን ቀጠና ቢዝነስ ዲቨሎፕመንትና ኦፕሬሽናል ማናጀር አቶ የሺዋስ ብዙአየሁ በበኩላቸው ባንኩ 74 ትራክተሮች ገዝቶ ለአርሶ አደሮች ማስረከቡን ገልጸዋል።

ለዚህም 259 ሚሊዮን ብር ብድር መስጠቱን ጠቅሰው፤ ባንኩ የተንዛዛና ውጣ ውረድ የበዛበትን አሰራር በማስወገድ በአርአያነት አርሶ አደሮችን እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

"አምባሰል ንግድ ሥራዎች ድርጅት ከክልሉ መንግስት በተመደበ 6 ሚሊዮን ዶላር የተለያዩ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ ውል ወስዶ እየሰራ ነው" ያሉት ደግሞ የድርጅቱ የባህር ዳር አቢይ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አበረ ይንገስ ናቸው።

የተመደበውን ዶላር በመጠቀም በሦስት ወር ውስጥ 63 ትራክተር፣ 65 ማረሻዎች እንዲሁም 8 ሺህ 700 የውሃ ፓንፖችን ለማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።

"የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ በርካታ ውጣ ውረድ ቢኖርም የገጠሙ ችግሮችን በመቋቋም ቴክኖሎጂዎቹን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ተችሏል" ብለዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ የክልልና የዞን ግብርና ዘረፍ አመራሮች፣ የፋይናነስ ተቋማትና አቅራቢ ድርጅቶች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም