ቀጥታ፡

የዋጋ ግሽበትን ለመከላከልና ለመቋቋም ድጎማን ጨምሮ በመንግስት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2015(ኢዜአ)፦ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከልና ለመቋቋም ድጎማን ጨምሮ በመንግስት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 28ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በ2015 በጀት ዓመት የመንግስት የስራ አፈፃፀም ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

የምክር ቤት አባላቱ መንግስት በተለይም የውጭ ጫናን ተቋቁሞ በሁሉም መስክ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን አድንቀው የዋጋ ግሽበት፣ የኑሮ ውድነት፣ የሰላምና ጸጥታ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
 
በምላሽና ማብራሪያቸውም በተለይም ኢኮኖሚውን በሚመለከት የመጀመሪያው የሃገር በቀል ማሻሻያ የግሉን ዘርፍ ማነቃቃት  ላይ ማተኮሩን ጠቅሰዋል።


ለፈጠራ፣ ለስራ አጥነትና የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን ለማስተካከል ዓላማ ያደረገና ምርታማነትን በማሳደግ የአገርን እድገት ለማስቀጠል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

እየተሻገሩ የመጡ የአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶች ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ተጨምረውበት ችግሩ ቢወሳሰብም በኢኮኖሚው  ረገድ  እመርታ መታየቱን  ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በሚቀጥለው ዓመት የዓለም እድገት 1 ነጥብ 4 እንደሚሆን ሲገምት የኢትዮጵያ አድገት 6 ነጥብ 4 እንደሚሆን ተንብዮ በፈጣን እድገት ላይ ካሉ የዓለም አገሮች ተርታ አስቀምጧታልም ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ ስንዴን ጨምሮ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪው ዘርፍም በጥሩ መነቃቃትና የእድገት ሂደት ላይ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃይል ልማትና የአገልግሎት ዘርፉም እድገት አምጥቷል ብለዋል። 

የዋጋ ንረት በዓለም ላይ "ወረርሽኝ" ሆኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ሲሉ አስረድተዋል።

በመሆኑም ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር ለመከላከልና ለመቋቋም የተለያዩ ተግባራትን መከናወናቸውን ጠቅሰው በማዳበሪያ፣ ነዳጅና ሌሎችም ላይ መንግስት ድጎማ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በዚህም የዋጋ ግሽበቱን ከ37 በመቶ ወደ 30 ዝቅ ማድረግ መቻሉን አስታውሰው በቀጣይም ለመቀነስና ለመቆጣጠር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል። 

በኢትዮጵያ ለውጡ ሲመጣ የእዳ ጫና 59 በመቶ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ 38 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ከ30 በመቶ በታች ለማድረስ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም