ቀጥታ፡

" ዓለም አቀፋዊ አጋርነት እና ትብብርን ለማጠናከር የፖለቲካ ቁርጠኝነት ወሳኝነት አለው "- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2015(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት እና ትብብርን ለማጠናከር የፖለቲካ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

በአምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአዘርባጃን ባኩ ከተማ እየተካሄደ ባለው የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ ( ናም) የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው ።

አምባሳደር ምስጋኑ የንቅናቄውን የሚኒስትሮች ስብሰባ እየተካሄደ ያለው ዓለም ውስብስብ በርካታ ፈተናዎች በተጋረጠባት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።

እርስ በእርስ በተሳሰረ ዘርፈ ብዙ ቀውስ ወቅት ከተለመደው አካሄድ በመውጣት አዲስ እይታ እና ሀሳቦች ማመንጨት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፋዊ አጋርነቶችን እና ትብብርን ለማጠናከር የፖለቲካ ቁርጠኝነት በጣም አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ሰላም የሰፈነበት እና የበለጸገ ዓለም የመፍጠር የጋራ ቃል ኪዳናችን አሁን ያለውን ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ስርዓት ካልተሻሻለ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት መሻሻል እንዳለበት ነው ያመለከቱት።

አምባሳደር ምስጋኑ በአየር ንብረት ለውጥ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችውን የአረንጓዴ ልማት እና በሰላም ማስከበር እየተጫወተች ያለውን ሚናም በጉባኤው ላይ አንስተዋል።

የአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ በበኩላቸው የአገራቸው የንቅናቄው ሊቀ መንበርነት "በባንዱንግ መርሆዎች" መሰረት ፍትሕ እና ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲሁም የአባል አገራትን ሕጋዊ ጥቅም አስጠብቋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ መስራች አባል እንደ መሆኗ የወደፊት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል መርህ ላይ ያተኮረ እና ውጤታማ የባለ ብዙ ወገን ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም እንዳላትም በጉባኤው ላይ መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም