የባህል ህክምናን በምርምር በማጎልበት በጤና ሥርዓት ውስጥ ያለውን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/ 2015 (ኢዜአ)  የባህል ህክምናን በምርምር በማጎልበት ከዘመናዊ ህክምና ጋር በማጣመር በጤና ሥርዓት ውስጥ ያለውን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ። 

በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው የጤና አውደ-ርዕይ ላይ በባህላዊ ህክምና ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በፓናል ውይይቱ በኢትዮጵያ የባህል ህክምና በሳይንሳዊ ምርምር አለመታገዙ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም እንዳላስገኘ የተገለጸ ሲሆን ክፍተቶችና ተግዳሮቶችም ተነስተዋል።

በዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የተመዘገቡና በገበያ ላይ የዋሉ የባህል መድሃኒቶች አለመኖር፣ በቤተ ሙከራ ደረጃ አለመፈተሽ የባህል ህክምና ላይ ተግዳሮት መሆናቸው ተገልጿል።  

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች የባህል መድሃኒቶችን ለማምረት ያላቸው ፍላጎት አናሳ መሆን የዘርፉ እድገት ማነቆ መሆኑን በፓናል ውይይቱ ተጠቅሷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ትምህርት ቤት መምህር ፕሮፌሰር አርዓያ ሃይመተ በተለይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ የባህል ህክምናን በምርምር በማጎልበት ከዘርፉ የሚጠበቀውን ጥቅም ማግኘት ይገባል ብለዋል።


 

በመሆኑም ለአገር በቀል እውቀቶች ትኩረት በመስጠት በጤና ሥርዓት ውስጥ ያለውን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ ነው ያነሱት። 

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ አቶ ሙላቱ ሲሳይ፤ ለመድሃኒት የሚውሉ የተለያዩ እጽዋትን መጠበቅና መንከባከብ፤ ፈዋሽነታቸውን በቤተሙከራ ማረጋገጥ፣ በባህል ህክምና ለተሰማሩ ሙያተኞች ስልጠና መስጠት እንደሚገባ ገልፀዋል።

የባህል መድሃኒት አዋቂዎች በጤና ስርዓቱ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ያሉት ደግሞ ዶክተር ጌታቸው አዲስ ናቸው።

አቶ ከማል ከድር ሌላኛው አስተያየት ሰጪ  የባህል ህክምናን ከዘመናዊ ህክምና ጋር በማጣመር በምርምር ማገዝ ባለመቻሉ በበቂ ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ተናግረዋል።

ይህን ሁኔታ ለመቀየር ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በበኩላቸው፤ መንግስት ከሌላው ጊዜ በተሻለ መንገድ የባህል ህክምናን በምርምር በማጎልበት በጤና ሥርዓት ውስጥ ያለውን ሚና ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም የባህል ህክምናን በአገር በቀል እውቀት ማጎልበት የሚያስችል የስትራቴጂክ አቅጣጫ አስቀምጦ እየተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ በአርማወር ሀንሰን የምርምር ተቋም ለባህል ህክምና የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

 

 

   

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም