ቀጥታ፡

የኢትዮ-ጅቡቲ የህዝብ ለህዝብ ወዳጅነት ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር ረገድ በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

  አዲስ አበባ ሰኔ 28 / 2015(ኢዜአ) ፡- የኢትዮ-ጅቡቲ ዘመን ተሻጋሪ የህዝብ ለህዝብ ወዳጅነት ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር ረገድ በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

የኢትዮ-ጅቡቲ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የስራ ኃላፊዎች፣ የጂቡቲ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ዴኤታ ሲራጅ ዑመር የተመራው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን፣ አምባሳደሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ የኢትዮጵያና ጁቡቲ ህዝቦች በባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ እና ማህበራዊ እሴት የተሳሰሩ ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት በወንድማማችነትና እህትማማችነት የተቆራኘ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለሁለቱ አገራት ህዝቦች የረጅም ጊዜ ግንኙነት መጎልበት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ጠቁመው፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ዘመን ተሻጋሪ የህዝብ ለህዝብ ወዳጅነት ለቀጣናዊ ትብብር በአርዓያነት የሚጠቀሰው መሆኑን አንስተዋል።

የሁለቱ አገራት ህዝቦች ትስስር ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበው፤የጅቡቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አዲስ አበባ መገኘቱም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የጂቡቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑክ መሪና የአገር ውስጥ ሚኒስትር ዴኤታ ሲራጅ ዑመር፤ ለልዑካን ቡድኑ የተደረገው አቀባበልና ዝግጅት የሁለቱን አገራት ህዝቦች የቆየ ወዳጅነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በአገራቱ መካከል ያለውን መልካም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር ለማስቀጠል በቁርጠኝነት የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ፀኃፊ  ዶክተር ወርቅነህ ገበየውን በመወከል ንግግር ያደረጉት የኢጋድ የፍልሰተኞች ፖሊሲ ትግበራ ፕሮጀክት አስተባባሪ የምስራች ብናልፈው፤ ሁለቱ አገራት ግንኙነት ከቀደምቱ የባቡር መስመር መሰረተ ልማት ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ገልጸዋል።

የባቡር መስመሩም የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ቤተሰባዊ ትስስር በማሳለጥ የማይተካ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

ኢጋድ በአባል አገራቱ መካከል ኢኮኖሚያዊ ውህደት እና የሰዎች በነጻነት መዘዋወር እንዲጠናከር የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የሰዎች ነፃ እንቅስቃሴ ፕሮቶኮል በኢጋድ አባል አገራት መጽደቁን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያና እና ጅቡቲ ሕዝቦችን ግንኙነት፣ ቀጣናዊ ፍልሰት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮን የሚዳስሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጹሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም