ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው- የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር

ጋምቤላ  ሰኔ 28 / 2015(ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ  እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኬሊ ክልመንትስ አስታወቁ።

ምክትል ኮሚሽነሯ ከስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይና ከሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የጀዌይ የስደተኛ መጠለያን ተመልክተዋል።


 

በዚህ ወቅት የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሯ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በስደተኞች ዙሪያ የወጡ የህግ ማቀፎችን ተግባራዊ በማድረግ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ረገድ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሀገር ናት።

የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ተቀብለው ሲያስተናገዱ በህዝባቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ነው የሚያሰቡት ብለዋል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ያለው ተጽዕኖ እንደሚፈጥሩ ሳይሆን አበርክቶ እንዳላቸው አድርጋ በመቀበል አስፈላጊውን ጥበቃና ሰብአዊ ድጋፍ እየሰጠች መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለስደተኞች እየሰጠች ያለው ጥበቃና ከለላ በተምሳሌትነት የሚጠቀስና እውቅና ሊቸረው የሚገባ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በበርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ውስጥም ሆና በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው የሚመጡ ስደተኞችን ተቀብላ እያስጠለለች እንደምትገኝ ተናግረዋል።


 

በቀጣይም ይኸው ተግባር ተጠናከሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል። 

የዕለቱ ምልከታ  ዓላማ የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን ተቀብሎ እያደረገ ያለውን ጥበቃ፣ ሰብአዊ ድጋፍና ከበጀት እጥረት ጋር ተያያዞ እያጋጠመ ያለውን ችግር በማየት  የመፍትሄ ሀሳብ ለመሻት መሆኑን አስታውቀዋል።

ከስደተኞች መካከል ሚስተር ጀምስ ቱት በሰጡት አስተያየት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ተቀብሎ እያደረገላቸው ያለው ጥበቃና ማህበራዊ አገልግሎቶች በእጅጉ የሚመሰገን ነው ብለዋል።

በተለይም በትምህርት ዘርፍ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ እየሰጠ ያለው የትምህርት ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና የሚቸረው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት በተለይም ልጆቻቸው የትምህርት እድል እንዲያገኙ በማድረግ በኩል እያደረገላቸው ያለው ድጋፍ በእጅጉ የሚደነቅ ነው ያሉት ደግሞ ሌላዋ ስደተኛ ሚስ ኛዌች ሮይ ናቸው። 

በጋምቤላ ክልል ባሉ ሰባት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች 383 ሺህ ስደተኞች እንደሚገኙ  ከስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም