ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልልነት ህዝበ ውሳኔዎችን በስኬት ማካሄዱ ጠንካራና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት እየተገነቡ መሆኑን ማሳያ ነው-ፌዴሬሽን ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልልነት ህዝበ ውሳኔዎችን በስኬት ማካሄዱ ጠንካራና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት እየተገነቡ መሆኑን ማሳያ ነው-ፌዴሬሽን ምክር ቤት
አዲስ አበባ ሰኔ 28/ 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልልነት ህዝበ ውሳኔዎችን በስኬት ማካሄዱ ጠንካራና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት እየተገነቡ መሆናቸውን ተጨባጭ ማሳያ ነው ሲል የፌደሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።
ምክር ቤቱ ይህን ያለው አዲስ የተመሰረተውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን የህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብእሸት አየለ በስድስት ዞኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች የተከናወነውን የህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም ማጠቃለያ ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ቦርዱ ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ነጻና ገለልተኛ በመሆን የዜጎችን የመወሰን መብት በማረጋገጥ ጠንካራ ተቋም እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
መንግስት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት አንደኛው ግቡ አድርጎ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም በገለልተኝነት የሄደበት ርቀት ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያበረክትና ለቀጣይ ምርጥ ተሞክሮ እንደሚሆን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከስድስተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ጀምሮ ህዝበ ውሳኔዎችን በገለልተኛነት ማከናወኑ ለዴሞክራሲ መጠናከር መሰረት እንደሚጥል በመጠቆም።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፤ ቦርዱ ሙያን መሰረት ያደረገ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ተቋም መሆኑን በተጨባጭ እያሳየ ነው ብለዋል።
የቦርዱ መጠናከርም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ጠንካራና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት የተቀመጠው አቅጣጫ በተያዘው አግባብ እየተፈጸመ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ያደረገው ህዝበ ውሳኔ ተቋሙ እየተጠናከረ ለመምጣቱ ምስክር መሆኑንም ተናግረዋል።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ምርጫው ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲ ሆኖ መካሄዱን ምክር ቤቱ በቅርበት መከታተሉን ገልጸዋል።