ማኅበረሰብ አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ሥርዓት የጤና ኤክስቴንሽን አሠራርን በማዘመን ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማኅበረሰብ አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ሥርዓት የጤና ኤክስቴንሽን አሠራርን በማዘመን ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 28/ 2015 (ኢዜአ) ማኅበረሰብ አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ሥርዓት የጤና ኤክስቴንሽን አሠራርን በማዘመን ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው ብሔራዊ የጤና ኤግዚቢሽን ከሰኔ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለሕዝብ ክፍት ሆኗል።
በአውደ-ርዕዩ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነች ያለውን ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶች እንዲሁም የጤናው ዘርፍ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የሚያሳዩ ቴክኖሎጂዎች ቀርበውበታል።
በኤግዚቢሽኑ በቴክኖሎጂው መስክ ከቀረቡት መካከል የማኅበረሰብ አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ሥርዓት ይገኝበታል።
በኢትዮጵያ በጤና ኤክስቴንሽን ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ቢቻልም ከመረጃ አሰባሰብና አያያዝ ጋር በተያያዘ ሰፊ ክፍተት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
በ2008 ዓ. ም በአገር ውስጥ የበለጸገውና የዛሬ አራት ዓመት ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የማኅበረሰብ አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ሥርዓት እስካሁን በ7 ሺህ 800 ጤና ኬላዎች 20 ሚሊየን ሰዎች በሲስተሙ መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
በጤና ሚኒስቴር የዲጂታል ጤና የሥራ ክፍል ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳዊት ብርሃን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የማኅበረሰብ አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ሥርዓት የጤና ኤክስቴንሽን ሥራ በቴክኖሎጂ የሚደገፍበት አሠራር መሆኑን ገልፀዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን ሥርዓት እስከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ድረስ የጤና አገልግሎት የሚሰጥበት ፕሮግራም መሆኑንም አንስተዋል።
ቴክኖሎጂው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ለአገልግሎት በሚሰማሩበት ወቅት ሥራዎቻቸውን በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚከውኑበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂው ባለሙያዎቹ የቤተሰብ የጤና ሁኔታ ክትትልን ከወረቀት ወደ ኮምፒዩተር ቋት ለማስገባት ያስችላቸዋል ብለዋል።
የማኅበረሰብ አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ሥርዓት አገር አቀፍ የሆነ ሲስተም መሆኑን እና በመላው አገሪቱ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ከአባወራ ጀምሮ ያሉ መረጃዎችን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሁሉም ክልል በዚህ ሲስተም የመመዝገብ ሥራዎች የተጀመሩ መሆናቸውን እና በተለያየ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቀጣይም ከእነዚህ መረጃዎች በመነሳት የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጡን እንደሚያሳልጥ ገልፀዋል።
ሲስተሙን ሙሉ ለሙሉ በመላው ሀገሪቱ ለመተግበር የቴሌኮም መሠረተ-ልማት፣ የታብሌት እና የፋይናንስ እጥረት እንደወሰነውም ነው ያመላከቱት።
በምስራቅ ሸዋ ሉሜ ወረዳ የቢዮ ጤና ጣቢያ የጤና ባለሙያዋ ሲስተር የሸዋለም ጉታ ሥርዓቱ በጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልፃለች።
ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ይጠቀሙበት የነበረው የወረቀት ቅፅ ሥራውን ውስብስብና አድካሚ እንዲሆን ማድረጉን ገልፀዋል።
ሥርዓቱ ባለው አባወራ መሠረት ዕቅድ ለማውጣት እንዲሁም የውሸት ሪፖርት መከላከልን እንዳስቻለም ተናግራለች።
የእያንዳንዱ ተገልጋይ መረጃ በጣት አሻራ እንደሚያዝ እና ሕክምናው ሲጠናቀቅ መረጃው በቀጥታ ወደ ጤና ሚኒስቴር የመረጃ ቋት የሚገባ መሆኑን ገልፃለች።
ይህም መረጃው ሚስጥራዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲያዝ ማድረጉን እና ሥርዓቱ እስከ ሪፖርት ድረስ ያሉ መረጃዎችን እራሱ እያዘጋጀልን ይገኛል ብላለች።
ሥርዓቱ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ እና የጤና ተቋማትን በማስተሳሰር ረገድም ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ገልፃለች።
በዚህ ትስስርም የህመም እና የሞት ምጣኔን ለመቀነስ እንደሚያስችል እና ምንም ዓይነት የመረጃ መዝረክረክ እንዳይኖር እንደሚረዳ ጠቅሳለች።