የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራዎች ውጤታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል- አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራዎች ውጤታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል- አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ
አዲስ አበባ ሰኔ 28/ 2015 (ኢዜአ) የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራዎች ውጤታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ተናገሩ፡፡
የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን የ7 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በተገኙበት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ እና የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተፈራርመዋል፡፡
አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ የሚካሄደው አገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ሚናው የጎላ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችንም አድንቀው፤ ይህም ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ አቅም መፍታት እንደምትችል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አካያ ህብረቱ በቀጣይም ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራዎች ውጤታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው፣ ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ስራዎች 35 ሚሊዮን ዶላር በጀት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
በጀቱም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚመደብ ጠቅሰው፤ እስካሁን ባለው ሂደት የዛሬውን ጨምሮ 12 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ቀሪ በጀቱን የማሟላቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች አጋር አካላት ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን እያደረጉት ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአገራዊ ምክክሩ ሂደት ውስጥ የዝግጅት ምዕራፉን በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መግባቱን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ናቸው፡፡
በዚህም የተሳታፊዎች ልየታ ስራው በተለይ በሲዳማና ሀረር ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታትም በሌሎች ክልሎች መሰል ስራዎች እንደሚከናወኑም ነው የገለጹት፡፡