ቀጥታ፡

ኢቢሲ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የዴሞክራሲ ባህልን የመገንባት ኃላፊነት አለበት- የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ 

አዲስ አበባ ሰኔ 28/ 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የሃሳብ ብዝኃነትንና የዴሞክራሲ ባህልን የመገንባት ኃላፊነት እንዳለበት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍሰሃ ይታገሱ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአዲስ አበባ ሸጎሌ አካባቢ አዲስ የተገነባውን ዘመናዊ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሚዲያ ኮምፕሌክስ በይፋ መርቀው ከፍተዋል።


 

በምረቃ ስነስርዓቱ ንግግር ያደረጉት የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ ሀገር ማለት የብዙ አምዶች ውቅር ናት ብለዋል።

ሀገር ጸንታ የምትኖረው በእያንዳንዳችን ምናብ ውስጥ በሚኖር የሀሳብ አንድነት እና በጋራ እሴቶች ጥንካሬ ልክ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የዚህ ምናብ ማዋቀሪያና የሀሳብ ማጠናከሪያ ቁልፍ መንገድ ደግሞ ሚዲያ ነው ሲሉ አመልክተው ሚዲያ ሀገርን በምናብ የሚገነባ እንዲሁም ህዝብ በኃሳብ፣ በባህልና በጠባይ የሚተሳሰርበት መሰናስል ነው ብለዋል።

ኢቢሲም በዚህ ረገድ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች በአካል ሳይተዋወቁ ወግና ባህላቸውን በማስተዋወቅ የላቀ ሚና መወጣቱን አብራርተዋል። 

ኢቢሲ  ከፖለቲካ እስከ ስፖርት፣ ከሃይማኖት እስከ ኪነጥበብ ከፓናፍሪካኒዝም ንቅናቄ እስከ አለም አቀፍ አጀንዳዎች የተላለፉበት መሆኑን አውስተው አሁንም ይህንን በማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢቢሲ ሀገራችን ወደ ቁልፍ የታሪክ ሂደት በምትሻግርበት በአሁኑ ወቅት የሀሳብ ብዝሃነትን በማስተናገድ የራሱን ሚና ለመወጣት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በነገ የትውልድ ግንባታ ውስጥ ኢቢሲ የላቀ ሚና ይጠበቅበታል ያሉት አቶ ፍሰሃ ዴሞክራሲን ለመትከልና ለማጽናት የሚያስፈልገውን የሃሳብ ብዝኃነት ለማስረጽ ግዙፍ ሚና ይጠበቅበታል ብለዋል።

የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ትርክትን በማጠናከር ጠንካራ ሀገር ለመፍጠርና ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለመገንባት ኢቢሲ እንደ ሀገራዊ ሚዲያ አይተኬ ኃላፊነት አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም