ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚሰሩ ተቋሞች ትልቅነቷን የሚመጥኑ መሆን አለባቸው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2015(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የሚገነቡ ተቋማት ትልቅነቷን የሚመጥኑ ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን(ኢቢሲ) የሚዲያ ኮምፕሌክስ መርቀው ከፍተዋል።

በዚህ ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ኢትዮጵያ ትልቅ ሃገር ናት፣ ጥንታዊት ሃገር ናት ታሪካዊ ሃገርም ናት” ያሉ ሲሆን ይሄንን ትልቅነቷን የሚመጥኑ ተቋማት ሊኖሯት እንደሚገባም ገልጸዋል።

May be an image of 10 people and newsroom

ኢቢሲ እንደ ዕድሜውና እንዳገለገለው ልክ ትልቅ ተቋም እንዳልነበረ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋሙ ይሄንን የሚመጥን እንዲሆን እምነቱ እንዳላቸው ተናግረዋል።

“ይሄ የኛ ሃገር ነው ለጊዜው የምንመራው ወይም የምንሰራበት አይደለም ባለቤቶች ነን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የምንሰራቸው ተቋማት የኛ ብለን ነው የምንሰራቸው እኛ ለፍተን የምናመጣው ለውጥ እንጂ ቢሮ ተቀምጠን የምናመጣው ለውጥ አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት በርካታ ተቋማትን ወደ ትልቅነት የማምጣት ከፍተኛ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው ኢቢሲን ጨምሮ በመከላከያ፣ በኢትዮ ቴሌኮም በአየር መንገድና በሌሎችም የተከናወኑትን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ኢቢሲም በሚመጥነው ልክ በቴክኖሎጂ በሰው ሃይል ቢደራጅ የኢትዮጵያን ገጽታ በአፍሪካ ደረጃ መገንባት እንደሚችል ገልጸዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም